ላለፉት ተከታታይ ቀናት በርካታ ጥያቄዎችን ያነገቡ የቀድሞ ተዋጊዎች በትግራይ ሰልፎችን እያካሄዱ መሆኑን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴውን በመደገፍና በመቃወም አስተያያታቸውን ሰጥተዋል።
በዚህም ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በትግራይ ጦርነትን ከማስቀረት አኳያ ሰሞኑን እየተካሄዱ ያሉት ሰልፎች መበረታት እንዳለባቸው ሲገልጽ፤ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ ንቅናቄው መሪ የሌለውና እፍፍሉ የበዛ በመሆኑ ፓርቲያቸው እንደማይደግፈውና ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ሊቀመንበር አሉላ ኃይሉ ለረዥም ጊዜ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እና ስጋቶች መኖራቸውን አስታውሰው ተዋጊዎቹ ያስተጋቧቸውን መልዕክቶች በመዘርዘር አስተያየታቸውን ጀምረዋል።
ይህንንም “አሁን እየተነሱ ያሉት የደመወዝ፣ ጥቅማቅጥቅም ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ናቸው፤ በተጨማሪ ግን እኛ የአንድ ፓርቲ ሠራዊት አይደለንም፤ ህዝቡም ቢሆን እንደ በፊቱ እየተቀበለን አይደለም፤ ለእኒዘህ ጉዳዮች መልስ ስጡን በሚል ነው የተለያዩ አርሚዎች መንገድ እየዘጉ ጥያቄዎች እያቀረቡ ያሉት” ሲሉ አስቀምጠዋል።
አክለውም “ይህ በግልጽ የሚታየው ነው፤ ከጀርባ ደግሞ የህወሓት ክፍልፋዮች እጅ አለበት የሚል አለ፤ ነገር ግን የሴራ ትንተና እንደ መሆኑ መጠን ብዙም ማረጋገጥ አልቻልንም” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በትግራይ ተፈናቃዮች፣ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ሰላማዊ ሰልፍ ከማድረጋቸው አኳያ ሰሞኑን እየተካሄዱ ያሉት ሰልፎች ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ወይ ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ሰልፎች ሰለማዊ ሰዎች ያደረጓቸው እንደ መሆኑ መጠን በኃይል በትነውታል በማለት ያለፈውን በማስታወስ ለምላሻቸው ዳራ ጠቅሰዋል።
ይሁንና በተከታታይ ቀናት የሚስተዋሉትን የአደባባይ ሰልፎች የሚያካሂዱት “እነርሱ (ህወሓት) ከእኛ ጋር ነው ብለው ያሰቡት ኃይል ነው ጥያቄ እያቀረበ ያለው፤ ስለዚህም ጉልህ የሆነ ለውጥ አለው፤ ይህ ሠራዊት እምቢ ካለ እነዚህ ሰዎች በአጠቃላይ ወደግለሰብነት ይቀየራሉ” ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጡና ምክንያታቸውን ያስከትላሉ።
ምክንያቱም እንደእርሳቸው ገለጻ ምንም ነገር አይኖርም። በዕድሜም የገፉ በሆመናቸው፤ ሥርዓቱን ማቆየት ይችላሉ ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል። “ብቸኛውና የቀራቸው የመደበቂያ ኃይል ስለሆነ ከዚህ ቀደም በትግራይ ከተካሄዱት ጉልህ ልዩነት አለው” ብለዋል።
ፖለቲካዊ አንድምታውን በተመለከተ ሲያስረዱ ደግሞ በማይመለከተን ጦርነት አንሳተፍም የሚለው ግፊት ከህዝቡም አሁን ደግሞ ወደሠራዊቱም እየመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ስለዚህ ይህ መቀጠል አለበት፤ ሰላሙ እንዲጸና፣ ከሰሜንም ከደቡብም ወደጦርነት የሚገፉ ነገሮች ትግራይ የምትሸከመው አይደለም፤ ከዚህ አንጻር ሰላማዊ ሰልፎቹ የሚበረታቱ ናቸው” ሲሉም ለተቃውሞ ሰልፉ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
መፍትሔውን በተመለከተ አቅጣጫ ሲያስቀምጡ በፕሪቶርያው ዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት ትግራይ ውስጥ ሁሉንም አካታች መንግስት እንዲመሰረት፣ የትግራይ ችግሮች ከአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ፍላጎት እና ህልውና አንጻር ብቻ ሳይሆን ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት ከሆነ የተናጠል ውሳኔዎች አይወሰኑም፤
ስለዚህ ህዝቡን ወደችግር የሚወስድ ውሳኔ አይተላለፍም፤ በትግራይ ውስጥ ሁሉም ኃይሎች ወደጠረጴዛ መጥተው ሁሉንም አካታች መንግስት መመስረት ከተቻለ ችግሮችን መፍታት ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ አባል ገ/ጊዮርጊስ ግደይ በበኩላቸው፤ “ሰላማዊ ሰልፉን የሚያካሂዱት ወጣቶች ከጦርነቱ በኋላ የተሻለ ሕይወት ይኖራችኋል የሚል ቃል ተገብቶላቸው ነበር፤ ነገር ግን ዛሬ ላይ ያ ቀርቶ ጥቂቶች ብቻ ተጠቃሚ ሲሆኑ ቁጭት እና ብሶት የወለደው ተቃውሞ ነው” ብለዋል።
“አሁን እነዚህ ልጆች ብሶት አላቸው ለምንድነው ታድያ ያ ሁሉ ከትምህርታችን ከሥራችን ከሁሉ ነገር ተፈናቅለን ወደዚህ ገብተን እንግዲህ አሁን ምን አገኘን የሚል ብሶት አላቸው” ሲሉም አክለዋል።
ገ/ጊዮርጊስ ሲቀጥሉ “መንግስት የራሱ የሆነ የተደራጀ አቅም ወይም ሌላ ገለልተኛ አካል አደራጅቶ በእነዚህ በኩል ከመንግስት ጋር እንዲገናኘኑ ካላደረገ በስተቀር አሁን እየጠየቁ ያሉት ትናንት አሳስተው ወደ ጦርነት ያስገቡዋቸውን ሽፍቶች ነው” በማለት የህወሓትን አመራሮች ተችተዋል።
“ጦርነቱ አልፎ ጥቂት ሰዎች የሚዘርፉበት የቡድን እንጂ የማህበረሰብ ሥርዓት የለም” ብለዋል፡፡ እናም ያ ሀሉ መመስዋዕትነት የከፈልነው ለምንድን ነው ሲሉ? በመጠየቅ ላይ መሆናቸውም አመላክተዋል፡፡
“በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ሁሉንም ያዋቀረ መንግስት መቋቋም ሲገባው ያ ሳይሆን ሲቀር እና ጥቂቶች ብቻ የሚዘውሩት መሆኑ ብሶትን አዋልዷል” አቶ ገ/ጊዮርጊስ ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።
ተቃውሞ ውጤት ማምጣቱን በተመለከተ ግን ከሳወት ሊቀመንበር አሉላ ኃይሉ የተለየ አስተያየት ነው ያላቸው፡፡
“ይህ ሰልፍ መሪው ማን እንደሆነ አይታወቅም፤ ሁሉም በየፊናው ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፤ ጫካ የገባ አለ፤ ከተማ ውስጥ ተቃውሞ የሚያሰማ አለ” በማለት ንቅናቄው የሚመራው ባለመኖሩና ክፍፍሉ መብዛቱ ወደእርስ በእርስ ግጭት እንዳያመራ ያሰጋል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
“በመሆኑም የተደራጀ መሪ ወይም ዓላማ በሌለበት እንዲህ ዓይነት ሰልፍ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት በእኛ በኩል የለም ” ሲሉም ንቅናቄውን የማይደግፉት መሆናቸውን ግልጽ አድርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተቃዋሚ ሰልፈኞቹ የሚያነሱትን ጥያቄዎች ለማስፈጸም አስጠንቼዋለሁ ያለው ጥናት ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ ተሰምቷል።
አዲስ_ማለዳ