በነዳጅ የሚሠሩና አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተሽከርካሪዎች ዕጣ ፈንታቸው ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር ነው ሲል የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር ስታንዳርድ ፀድቆ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ኃላፊው፤ የኤሌክትሪክ መኪና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያም ከ100 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ወደ ገበያው ማስገባት ችላለች ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
በመጪዎቹ 10 ዓመታት ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች መካከል “95 በመቶ የሚሆኑትን የኤሌክትሪክ ለማድረግ” እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የኤሌክትሪክ መኪና ምርትን ለማፋጠን፣ የነዳጅ ወጪን ለመቀነስ እና አረንጓዴ ከባቢን ለመገንባት አቅዶ እየሠራ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ውስጥም ከ500 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።