የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ስምምነት መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ የስሪት አገር ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሰጥቷል።
ሰርተፊኬቱ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ እና ኬኒያ የኢትዮጵያ ምርት የሆኑ እቃዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት መሰረት ለሚልኩ ሁለት ድርጅቶች የተሰጠ ሲሆን ድርጅቶቹ ሰርተፊኬቱን ከጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እጅ በይፋ ተረክበዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ለእቃዎች ንግድ ታሪፍ ቅነሳ ወሳኝ መሳሪያ የሆነውን የስሪት ሀገር የምስክር ወረቀት (Certificate of origin) በአህጉራዊ ነጻ ንግድ ስምምነት ጽ/ቤት በተዘጋጀው የጥንቃቄ መስፈርት (Security Features) መሰረት ለህትመት የማብቃት እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡
የመጀመሪውን እና ሁለተኛውን የስሪት ሀገር ማረጋገጫ ሰርትፊትፍኬት Lampros Trading PLC በድምሩ 96 ሜትሪክ ቶን ነጭና ቀይ ቦሎቄ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ እና ሶስተኛውን የስሪት የስሪት ሀገር ማረጋገጫ ሰርተፍኬት Belayeneh Kinde Mekonnen 400.8 ሜትሪክ ቶን በቆሎ ወደ ኬንያ ኤክስፖርት በማድረግ በይፋ ኢትዮጵያ ንግዱን ጀምራለች፡፡
ኮሚሽነር ደበሌ በርክክብ ስነስርዓቱ እንደገለጹት፣ ይህ ስኬት እንዲመጣ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ባለድርሻ አካላትን በማመስገን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በቀጣይም በነፃ የንግድ ቀጠናው ማዕቀፍ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለሚልኩ ባለሀብቶች የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ስምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ54 የአፍሪካ ህብረት አገራት ተፈርሞ እ.ኤ.አ ከግንቦት 30 ቀን 2019 ጀምሮ ጽ/ቤቱን (AfCFTA Secretariat) በጋና አክራ ከፍቶ ወደ ትግበራ ሂደት የገባ በአባላት ብዛት ትልቁ ነፃ የንግድ ቀጠና ሲሆን የሀገራችንም የእቃዎች ንግድ ታሪፍ ኦፈር በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 574/2017 በይፋ መታወጁ የሚታወስ ነው።
(ጉምሩክ ኮሚሽን፣ መስከረም 28 ቀን 2018 ዓ.ም)