በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተመረቀው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ በሰዓት 60 ኪዩቢክ ሜትር ኦክስጅን የማምረት አቅም እንዳለው ተገለጸ። ፋብሪካው የሆስፒታሉንና የአካባቢውን የኦክስጅን አቅርቦት ለማሻሻል እንደሚያግዝም ተነግሯል።
የሆስፒታሉ ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ሙስጠፋ መሐመድ እንደገለጹት፣ ሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም የኦክስጅን ፍላጎቱን ለማሟላት በውጭ አቅራቢዎች ላይ ጥገኛ ነበር። ይህም በአቅርቦት፣ በወጪና በተደራሽነት ረገድ ተግዳሮቶችን ይፈጥር እንደነበር ጠቁመዋል።
የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካው መመረቅ ሆስፒታሉ የሚያስፈልገውን ኦክስጅን በራሱ እንዲያመርት በማስቻል፣ የአቅርቦት መቆራረጥን ለመቀነስ፣ የማጓጓዣ ወጪንና ጫናን ለማቃለል እንዲሁም የሕክምና አገልግሎቱን በተረጋጋ ሁኔታ ለማቅረብ እንደሚያግዝ ዶክተር ሙስጠፋ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሆስፒታሉ በአካባቢው ለሚገኙ ሌሎች የጤና ተቋማት ኦክስጅን የማቅረብ ዕድል እንደሚኖረው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ይህም የአካባቢውን አጠቃላይ የጤና አገልግሎት አቅም ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፣ ወራቤ ሆስፒታል በዓመት ለኦክስጅን ሲሊንደር መሙያ አገልግሎት 10 ሚሊዮን 470 ሺህ ብር ገደማ ያወጣ ነበር።
