በአማራ ክልል ባለፉት 9 ወራት ዉስጥ 176 ሰዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል አስታወቀ።
በሆስፒታል የድገተኛ ክፍል ሀኪም ዶ/ር ጓዴ ተዋበ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፥ ” ራሳቸው የሚያጠፉ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መጥቷል ” ብለዋል።
” በየቀኑ አንድ ራሱን የሚያጠፋ ወጣት ወደ ሆስፒታሉ ይመጣል ” ያሉት ዶ/ር ጓዴ ” በአብዛኛቹ መድሃኒትም ለበረሮና ለአይጥ ማጥፊያ ተብሎ የሚሸጠውን metalophophide ተብሎ የሚጠራውን ፀረ ተባይ ማጥፊያ መድሃኒት ነው የሚወስዱት ” ብለዋል።
በ9 ወራት ውስጥ 176 ያህል ወጣቶች ራሳቸውን አንዳጠፉ የሚናገሩት ዶ/ር ጓዴ አብዛኛዎቹ ከ15 እስከ 30 አመት የአድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።
” ተጎጂዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸው በምርመራ ነው የሚገኘው ” ያሉ ሲሆን ” በተጨማሪ ከቤተሰቦቻቸው የሚገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በራሳቸው ላይ አደጋውን ከመፍጠራቸው በፊት ይናገሩት የነበረውን ቃላት እንዲሁም መድሃኒቱን ከወሰዱ በኃላ ከአጠገባቸው የሚገኘው የወሰዱት መድሃኒት መያዣ ራሳቸውን ለማጥፋታቸው ማረጋገጫ ነው ” ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ መድሃኒቱን ከወሰዱ በኃላ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መጥተው የትረፉ ወጣቶች ቃለ መጠየቅ ሲደረግላቸው ራሳቸውን ለማጥፋት ያነሳሳቸው ከቤተሰብ እና ከፍቅር ጓደኛ ጋር የሚደረግ ጊዜያዊ ግጭት እንዲሁም ‘ ኑሮ መረረን ‘ የሚሉ ምክንያቶች እንደሚሰጡ ዶ/ር ጓዴ ተናግረዋል።
” በተለይ የፀረ ተባይና ተዋሲያን ማጥፊያ መድሃኒቶች ከተፈለገው አላማ ውጭ እየዋሉ ስለሆነ ገበያ ላይ በስፋት እንዳይገኙ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ አለበት ” ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
የስነ ልቦና ባለሙያው ስለ ራስን ማጥፋት ምን አሉ ?
በፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስነ አዕምሮ ባለሙያ ዶ/ር ማቲዮስ ሚሳኔ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እደተናገሩት ፤ በአለም ላይ ከ90 እስከ 95 መቶ ያህሉ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች መንስኤው የአእምሮ ጤና እክል ሲያጋጥም ሲሆን ቀሪዎቹ 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከፍቅር ጓደኛ፣ ከቤተሰብ ጋር በሚደረግ ጊዜያዊ ግጭት ይከሰታል።
” የአእምሮ ጤና መታወክ መነሻው ጭንቀት፣ ድብርት ፣ ለችግሮች ወይም ለነገሮች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት አለመቻል ናቸው ” ብለዋል።
ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች የሚያሳዩትን ምልክቶች በተመለከተም አብራርተዋል።
– ብቸኛ መሆን
– መጨነቅ
– ድብርት ውስጥ መግባት
– ስለ ራስ ማጥፋት በተደጋጋሚ መናገር
– ” መኖር የለብኝም ሳልወለድ ብቀርስ ” የሚሉ ንግግሮችን መናገርና ተስፋ የመቁረጥ ምልክቶችን ያሳያሉ ሲሉ ዶክተሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም እንደ ገመድ ፣ መርዝ እና ስለታማ ነገሮችን በአጠገባቸው/በአካባቢያቸው አለማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
መፍትሄው የስነ ልቦና ምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ፤ የአእምሮ ጤና አገልግሎት ወደሚሰጥበት ህክምና መውሰድ ውጥረትና ጭንቀትን የሚቀንሱ ተግባራትን ማከናወን እንደሆነ ጠቁመዋል።
የቅርብ ሰዎችደግሞ የስሜትና የባህሪ ለውጦችን መከታተል እንዲሁም ንግግሮችን ችላ አለማለት እንዳለባቸው መክረዋል።
የሃይማኖት አባቶች ራስን ስለ ማጥፋት ምን አሉ ?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባህር ዳር ሃገረ ስብከት ዋና ፀሃፊ መልዓክ ብርሃነ ፍሰሃ ጥላሁን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፥ ” የሰው ልጅ ተስፋ የሚቆርጠው ከፈጣሪ ሲርቅ ነው። ከፈጣሪ መራቅ ደግሞ የሞራል ዝቅጠት ያመጣል በዚህም በእግዚአብሔር አምሳል የፈጠረውን ማንነቱን አንዲንቀውና ክብር አንዲያጣ ያደርገዋል ” ብለዋል።
” ይህ የዳቢሎስ ስራ ነው ዳቢሎስ ደግሞ ተስፋ አስቆርጦ ወደ ራሱ ግዛት የሚስበው ከሞት በኃላ ያለውን ዘላለማዊ ህይወትእንዳይወርሱ በማሰብ ነው ” ሲሉ ገልጸዋል።
” ይህን ረጅም የሰይጣ እቅድ ወጣቱ እየተረዳው ስላልሆነ በትንሽ ያውም ሊስተካከል በሚችል ነገር ክቡር የሆነውን ህይወቱን ያጠፋል ወጣቱ የሰይጣንን አጀንዳ መረዳት አለበት ” ሲሉ አስገንዝበዋል።
” በየትኛውም ሃይማኖቶች የሚገኙ መሪዎች ራስን ማጥፋት ሃጥያት መሆኑን ያስተምራሉ ስለዚህ ወጣቱ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲሰማው ወደ ሃይማኖት ተቋማት መሄድ አለበት ” ብለዋል።
” ከሃይማኖት አባቶች እግር ስር ሆነው ንሰአ መግባት የእግዚአብሔርን ቃል መማር መፀለይ አለባቸው ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
” ሁሉም ነገር የሚሳካው በእግዚአብሔር ፍቃድ በመሆኑ ወጣቱ በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ እምነቱን መጣል አለበት ” ሲሉም አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ባሕር ዳር