አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ በሆቴልና ሪዞርት ግንባታ ረገድ ወደ ድሬዳዋ ከተማ እየገቡ መሆኑን፣ የከተማዋን ከንቲባና ካቢኔውን አግኝተውም ቃል እንደተገባላቸው ዛሬ ገልጸዋል፡፡
የኃይሌ ሆቴሎች ሪዞርቶች ግሩፕ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ጋዲሳ ግርማ በበኩላቸው፣ ድሬዳዋ ላይ የሆቴልና ሪዞት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር ዛሬ ምሽት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡
ሻለቃ ኃይሌ፣ በድሬ ከተማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ “ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በየከተማዎቹ እየገነባን ነን፡፡ እስካሁን በአስር ከተሞች ተከፍተዋል፡፡ ሌላ ሦስት ደግሞ በግንባታ ላይ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ የድሬው 14ኛው ይሆናል” ብለዋል፡፡
“መምጣት ካለብን በጣም የዘገየንበት ቦታ ነው፡፡ ግን አሁን ድሬዳዋ እየገባን ነው፤ ክቡር ከንቲባውንም ካቢኔውንም አግኝተን በጣም ጥሩ ቃል ገብተውልናል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሥራው ቶሎ እንደሚጀመር ጠቁመው፣ “በየቦታው የሰራናቸውን ሆቴሎች አይነት አንዷን ድሬዳዋ እናስቀምጣለን ብለን አቅደናል፡፡ መጀመሪያ ስናጠና ቢዝነሱ እንዴት ነው ? የሚለውን ነው፤ ድሬዳዋም ከኢትዮጵያ ቀደምት ከተሞች አንዷ ነች፤ በቢዝነሱም” ነው ያሉት፡፡
ስለድሬዳዋው ሆቴል ግንባታ ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኃይሌ ሆቴሎች ሪዞርቶች ግሩፕ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ጋዲሳ ግርማ፣ “የቦታ ልየታና ገበያውን ለማየት ሂደን ነበር ዛሬ፡፡ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰሩ የመንግስት አካላት ቦታዎችን አሳይተውናል፤ ወደ ቀጣዩ ሂደት እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
ግንባታውን በቅርቡ የመጀመር እቅድ እንዳላቸው፣ በዚህ ቀን ይጀመራል የሚል ቀን ገና እንዳላስቀመጡ ገልጸው፣ “የመሬት ርክክብ ባለቀ በማግስቱ ግንባታ እንጀምራለን” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
የጎንደርና ደብረ ብርሃን ፕሮጀክቶችን እያጠናቀቁ በመሆኑ ቀጣዩ አቅጣጫ ወደ ድሬ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ጋዲሳ፣ “ደብረ ብርሃን ሆቴል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነው ያለው፤ በቀጣዮቹ ሦስት አራት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ የጎንደር ደግሞ ከሰባት ውራት እስከ አንድ አመት ይወስዳል” ብለዋል፡፡
በጎንደሩ ፕሮጀክት የጸጥታው ሁኔታ ምን አይነት እንቅፋት እንዳፈጠረባቸው ማብራሪያ ሲጠየቁም፣ በዚህ ረገድ አስተያየት አለመስጠትን መርጠዋል፡፡
@tikvahethiopia