በ43ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አጠቃላይ ጉባኤ የቦርድ አባል ለመሆን በእጩነት መቅረቧን ብሔራዊ ዩኔስኮ ኮሚሽን አስታውቋል።
በትምህርት ሚኒስትር እና የብሔራዊ ዩኔስኮ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሳማርካንድ፣ ኡዝበኪስታን እየተካሄደ በሚገኘው 43ኛው የዩኔስኮ አጠቃላይ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በዚህ ጉባኤ ላይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዩኔስኮ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አስቀምጠዋል።
በዚህም ከትምህርት፣ ከባሕል፣ ከአየር ንብረት ለውጥ እና የብዝሐ ሕይወት ዘርፍ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እየሰራቻቸው ያሉ ሥራዎችን ለጉባኤው አስረድተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት (ተመድ) የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የተነደፉ ስትራቴጂዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በዩኔስኮ ዘርፍ አምስት መርሃ ግብሮች እየተተገበሩ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት እንደሆነ፤ የብሔራዊ ዩኔስኮ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ አለሙ ጌታሁን ተናግረዋል።
ዋና ፀሐፊው በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዩኔስኮ አጠቃላይ ጉባኤ በትምህርት፣ ሣይንስ፣ ባሕል፣ ተግባቦትና መረጃ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ፤ አባል ሀገራትን ስለሚደግፍ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መድረክ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም ከጉባኤው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚደረጉበት ስለሆነ፤ ትልቅ ዋጋ ያለው ጉባኤ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ለመሆን በእጩነት መቅረቧን የተናገሩት ዋና ፀሐፊው፤ አባል ሆኗ መመረጧ በማንኛውም የቦርዱ ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ ያደርጋታል ብለዋል።
ዋና ፀሐፊው እጩ ሆነው ከቀረቡት ውስጥ 58 ሀገራት ብቻ የቦርድ አባል ሆነው ይመረጣሉ ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም 99 በመቶ ትመረጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ድምፅ መስጠት እና እንዲሰጥላት ማድረግ የምትችልበት ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በእነዚህ ምክንያቶች ኢትዮጵያ በዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አጠቃላይ ጉባኤ ልዩ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በዩኔስኮ የሚደረጉ የጉባኤ ተሳትፎዎች ብዙ መርሃግብሮች ተቀርጸው በተመሳሳይ ብዙ ችግሮች የሚፈታበት ስለሆነ የዘንድሮው አጠቃላይ ጉባኤ ተስፋ እንደተጣለበት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የተመዘገበውን የአኒያዋ ደንን ጨምሮ እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ 6 የባዮስፌር ሪዘርቮችን ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡
(አሐዱ ሬዲዮ)
