አማራን ለማጥፋት ይሞከራል እንጂ አይሳካም!

Date:

ከወርቁ ተስፋዬ

ሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ እኝህ ከቤተሰቦቻቸው የመጨረሻ ልጅ ሲሆኑ በአባታቸው የፈረስ ስም የሚጠሩ ሲሆን ጃገማ በኦሮምኛ ‹‹ኃይለኛ›› ማለት ነው፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ በዓደዋ ጦርነት የተሸነፈውን ሽንፈት ከአርባ ዓመታት በኋላ ቂሙን ለመበቀል ዘመናዊ መሳሪያዎችን እንዲሁም በዓለም የተከለከለ የጋዝ መርዝ በመያዝ በ1928 ዓ.ም በሀገራችን ወረራ በአካሄደበት ጊዜ በአፍላ የ15 ዓመት የእድሜ ጊዜያቸው በጠላት ላይ በፈፀሙት ጀብድ ‹‹የበጋው መብረቅ›› የሚል የአድናቆት ስም ያላቸው ናቸው፡፡

ከአምስት ዓመታት አርበኝነት ድል በኋላ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሰራዊት አባል ሆነው ለኢትዮጵያ አንድነት የከፈሉት አገልግሎት እና የትግል ውጤት እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ የአያታቸውን አደራ ተገንዝበው በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን የማስፈን ራዕይን ሰንቀው በመታገላቸው በተለይም በድፍን የአማራ ማኅበረሰብ ዘንድ እስከ አያታቸው ድረስ የአክብሮትና የአድናቆት የክብር ቦታ የተሰጣቸው አስተዋይ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ 

ነገሩ እንዲህ ነው ጃገማ ኬሎ የዘጠኝ ዓመት እድሜ ሳሉ በአያታቸው ቤት በቁጥር ከአምስት የማያንሱ እንግዶች ይመጣሉ፡፡ እነዚህ እንግዶች በአያታቸው ቤት ቤት ያፈራውን እህል ውሃ እየቀማመሱ ከቆዩ በኋላ የመጡበትን ዓላማ እንዲህ ብለው በዝርዝር ያስረዳሉ፡- ‹‹የአማራን ተወላጆች እናጥፋቸው፡፡ ለዚህም እርስዎ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ተሰሚነት እና ተቀባይት ስላለዎት ድጋፍዎትን ይሰጡናል ብለን ነው የመጣነው›› ብለው የልመና ትብብር ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል፡፡

ሁሉንም ነገር በእርጋታ ካዳመጡ በኋላ እሺ ለዚህ ሀሳባችሁ ከልጆቼ ጋር አብረን እንመካከርበት ብለው የልጅ ልጃቸውን ጃገማ ኬሎን ከቤት ስላዩት አባቱን እና አጎቶቹን በፍጥነት እንዲጠራቸው ያዙታል፡፡

ሁሉም ልጆቻቸው ከተጠሩ በኋላ ቤተ ዘመድ ከእንግዶች ጋር ይሰባሰባሉ፡፡ እንግዶቹም የመጡበትን ጉዳይ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አንድ በአንድ ዘርዝረው ያስረዳሉ፡፡

የጃገማ ኬሎ አያትም ወደ አብራክ ልጆቻቸው ዘወር ብለው ጉዳዮን እንዴት ታዩታላችሁ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ልጆቻቸውም በመደነቅ እና በመገረም ምላሽ ሊሰጧቸው ስላልቻሉ ወደ እንግዶቹ ዘወር ብለው አማራን ለመግደል ወይም ለማጥፋት የምትፈልጉበት ዋናው ምክንያት ምንድነው? ምንስ ተጨባጭ አሳማኝ ምክንያቶች አላችሁ? የአማራን ዘር ለማጥፋት ይቻላል ወይ? ይሳካልስ? የመሳሰሉት ጥያቄዎችን እያሽጎደጎዱ ካቀረቡላቸው በኋላ እሺ ሓሳባችሁን በጥቅሉ ልጋራ ድርጊታችሁንም ስሜታዊ ሁኜ ልደግፋችሁ፡፡

በመጀመሪያ ከቤቴ ጀምሩ፡፡ እህል ውሃ ያቀረበችላችሁ ባለቤቴ ላይ እንጀምር፡፡ ግደሏት ብለው የአይናቸውን ማረፊያ እና መመኪያ የሆኑ የልጅ ልጅ ያፈሩላቸውን የልጆቻቸውን ወላጅ እናት አሳያቸው፡፡ አነሱም ‹‹እሷማ ዘመዳችን የእኛ ዘር ነች፡፡ እንዴት እንገላታለን›› ሲሏቸው በረጅሙ ከተነፈሱ በኋላ ግርማ ሞገስ ያለውን የተረዥገዥገ ፂማቸውን እየጎተቱ በሉ እንግዲህ አድምጡ የባለቤቴ ዘር አማራ ነች፡፡

የእከሊት ባል የእከሌ ሚስት ማን አንስቼ የማንን ልተወው ዘራቸው አማራ ነው፡፡ ከዚህ ተወልደው ያደጉ የኦሮሞን ባህልና ወጉን ጠንቅቀው የሚያውቁ ቋንቋውንም አቀላጥፈው ስለሚናገሩ ነው፡፡ ስለዚህ ብለው ከእንግዶቹ ፊት የቴፍ አይነቶችን እንዲቀርቡላቸው አስደረጉ፡፡ በእነዚህ የጤፍ አይነቶች ለሰውነታችን፣ ለጉልበታችን ፣ለአስተሳሰባችን እና ለጤንነታችን የሚሰጡት ጥቅም የተለያዩ ናቸው፡፡

ሁሉንም ስለምንመገባቸው የፈረጠመ ጠንካራ ጉልበት እንዲኖረን፣ አስተሳሰባችን ጠለቅ ያለ የወደፊቱን አሻግሮ የሚመለከት ብሩህ አዕምሮ ያለን በሰውነት አቋማችንም ላይ የተስተካከለ ቅርጽ ያለን ጤነኛ አምራች ትውልድ እንድንሆን ያደርጉናል፡፡ እኛም ወደን አይደለም ከላይ እንደ ተለያዩ የእህል ጤፍ አይነቶች ለሰውነታችን እንደሚሰጡት ጥቅም ለብዙ ዓመታት  ኢትዮጵያዊያን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት ሳንከፋፈል በአምቻ ጋብቻ ተሳስረን በደም በሥጋ በአጥንት የተዋሕድን የአንድ ማህበረሰብ አንድ ሕዝብ የሆነው፡፡ በመሆኑም በጦርነትና በተያያዥ የእርስ በርስ ግጭቶች እና አለመረጋጋት ሳቢያ እጅጉን መጎዳዳት የለብንም፡፡ ያለበለዚያ ግን ይዋል ይደር እንጂ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ቀዳዳ መክፈት ነው፡፡

እኛ የኦሮሞ ተወላጆች እኮ እንኳን ወገኖቻችንን ልንገድል ቀርቶ ያሳደግነውን እንሰሳ አርደን ለመብላት የሚያስችል የጭካኔ ልብ የለንም፡፡ ለእንሰሳት እና ለአራዊት በራችን ደጅ ላይ ውሃ እና ወተት የምናስቀምጥ ደግ እና ሩህሩህ ሕዝብ ነን፡፡

ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ይህን የሰይጣን ሴራ እንዳታስቡ ብለው መክረው ዘክረው በባህላችን እና በወጋችን መሰረት ከትክሻቸው ያነገቡትን መሳሪያ መሬት ላይ አጋድመው መሳሪያውን እየተረማመዱ ይቅር ለእግዚአብሔር እንዲባባሉ አድርገው ሸኝተዋቸዋል፡፡

ከዚህ ታሪክ መረዳትና መገንዘብ የማይችሉ ያውም የሀገር ውስጡን ብቻ ሳይሆን የውጪውንም አለም ትምህርት ቀስመዋል የሚባሉት በዘመነ ህወሓት የአማራ ተወላጆችን በአርባ ጉጉ፣ በአሰቦት ገዳም በዘራቸው እየተመረጡ እንዲያልቁ ተደረገ፡፡ አሁን ደግሞ በብልጽግና የሥልጣን ዘመንም በተመሳሳይ ሁኔታ ያውም ከመቸውም በተጠናከረ ሁኔታ በአማራ ተወላጆች ላይ አሳዛኝና ዘግናኝ ድርጊቶች ቢፈፀምም አማራን ለማጥፋት ይሞከራል እንጂ ስለማይሳካ ከእንግዲህ ሁላችንም ከታሪክ እንማር፡፡ ታሪክ ይወቅሰናል፡፡ እንደ ጥንቱ አያቶቻችን ይቅር ተባብለን ከመጥፎ ድርጊቶች ራሳችንን እንቆጥብ ፤ እንራቅ፡፡ ሥልጣን እና ጊዜ ኃላፊ ነው፡፡ ሀገር እና ሕዝብ ግን ኃላፊ አይደለም፡፡  

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...