አባ መላ (በእውቀቱ ስዩም)

Date:

ሰሞኑን ያሜሪካን ፖለቲካ እተነትናለሁ፤ ለጥቂት ቀን ነው፤ ታገሱኝ!

ምንድነው የሆነው?

ዋናውን ሰውየ ስልጣን እንዲገርብ የረዳው ኤለን ማስክ እሚባለው ቢሊኒየር ነው፤ ዋናው ሰውየ ፕሬዚዳንትነቱን ዳግመኛ ሲረከብ ለኤለን ማስክ ከስልጣኑ ሸርፎ ሰጠው፤ ቢሊኒየሩ ስልጣኑን ተጠቅሞ በወር ደመወዝ የሚኖሩ ሰዎችን ከስራ መቀነስ ጀመረ፤ በተለይ ወንድሜን ሀብታሙ ስዩምን ጨምሮ ብዙ ወዳጆቼ የሚሰሩበትን VOAን በመዝጋቱ ተቀይሜው እንባየን ወደላይ አፈናጥቄበት ነበር፤ እንባየ ወደ ታች ሲመለስ መአት ይዞ ነው የተመለሰ፤ ሁለቱ ሀያላን ተደባበሩ፤ አሁን ትራምፕ፥ ኤለን መስክን እንዴት ካገር ላባርረው በሚለው ላይ እየመከረ ነው’ ከነሀብቱ ላባርረው? ወይስ ኮፍያውን እና የሺሻ እቃውን ብቻ ይዞ ይውጣ በሚለው ዙርያ እያሰበበት ነው፤

እዚህ ላይ የአባ መላ ጨዋታ ነው ትዝ ያለኝ ፤

ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ(አባ መላ) ባጤ ምኒልክ የተሾሙ የጦር ምኒስትር ነበሩ፤ መልካቸው ከመረራ ጉዲና ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ በፖለቲካዊ ብልጠት ግን የሚመስላቸው አልተገኘም፤
ጃንሆይ ቀዳማዊ ሀይለስላሴን ወደ ዙፍን እንዲወጡ የረዷቸው እኒህ አባ መላ ነበሩ፤

ያኔ ጃንሆይ ተፈሪ መኮነን በሚባልበት ዘመን ብዙ ተቃዋሚ ነበረው፤ ተቃዋሚዎቹን የሚዘርርበት ዘዴ ሲፈልግ ወደ አባ መላ ቤት ጎራ ይላል ፤ አባ መላ፥ ድንክ አልጋ ላይ
ተቀምጠው ፥ ሪህ የቆረጠመውን እግራቸውን በብር ለብ ያለ ውሀ በተሞላ የብር ገበቴ ውስጥ ዘፍዝፈው፥ ይቀበሉታል ፤ ምክሩን ተቀብሎ እጅ ነስቶ ይመለሳል፤

ተፈሪ ስልጣን ካደላደለ በሁዋላ አንድ ቀን፥

“ ልኡል ተፈሪ ፈልጌህ ነበር” ብለው ላኩበት

“ ከፈለጉኝ ለምን አይመጡም ? “ ብሎ መለሰላቸው፤

“እኔ ነኝ እምመጣ?”🤔 አሉ አባ መላ፤

ተፈሪ “ አዎ እርስዎ! ቆይ ማነኝ ብለው ነው እሚያስቡት ግን ?🙁 እናትዎን ! “ ሊል እንደማይችል የታወቀ ነው፤

በተለመደው በጨዋና አነጋገር “ ከፈለጉኝ እኔ ያለሁበት ቦታ ይምጡ” ብሏቸዋል ይባላል፤
አባ መላ ይህንን ሲሰሙ ተክዘው ምን አሉ፤

“ ወይ ጉድ ! ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ አቃተን”

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...