12ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግና ፋሽን ዊክ እንዲሁም 15ኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ በይፋ ተከፈቱ። ከ70 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ ኩባንያዎች የተሳተፉበት መድረኩ፣ የአፍሪካን የቆዳ፣ የጨርቃጨርቅና የፋሽን ምርቶች ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅና የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
አውደ ርዕዮቹ ለአራት ቀናት የሚቆዩ ሲሆን፣ ከ6 ሺህ በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና ባለሀብቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመድረኩ የቆዳና የጨርቃጨርቅ ምርቶች፣ የማምረቻ ማሽነሪዎች፣ የፋሽን ፈጠራዎች እንዲሁም የሰው ሠራሽ አስተውሎትና የኢ-ኮሜርስ ሚና ላይ ውይይቶች ይካሄዳሉ።
እነዚህ አውደ ርዕዮች ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ አምራቾች ከዓለም አቀፍ ገዢዎችና ባለሀብቶች ጋር የሚገናኙበት ዕድል ይፈጥራሉ። ይሁንና የመድረኩ ስኬት በተሳታፊዎች ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ተጨባጭ የንግድ ስምምነቶች፣ የሥራ ዕድሎችና የምርት ሽያጭ ምን ያህል እንደሚቀየር ላይ ይመሠረታል።
