“ኢትዮጵያዊ ራሱን ለባርነት አሳልፎ አይሰጥም”

Date:

አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን

ዮሐንስ መኮንን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኪነ-ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በከተማ እና በኪነ-ሕንጻ እና ቅርስ እንክብካቤ፤ በአካባቢ ዕቅድ (Environmental Planning) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለማግኘትም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት በዲዛይን ማማከር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በሥራ ዓለም ውስጥ ቆይተዋል፡፡ በዛሬው የኢትዮጵያዊነት ዓምዳችን እንግዳችን ኾነው ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አንጻር ለሰነዘርንላቸው ዐሥር ጥያቄዎች የሚከተሉትን ምላሾች ሰጥተውናል፡፡  

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት በእርሶ እይታ እንዴት ይገለፃል?

ዮሐንስ፡- ኢትዮጵያዊነትን በብዙ መልኩ የሚያዩት ሰዎች እንዳሉ እገነዘባለሁ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያዊነትን የተለያየ ማንነቶች በመዋጮ የሠሩትና በማንኛውም ጊዜ መዋጮው ወይም ኮንትራቱ ሊቋረጥ የሚችል ዓይነት አድርገው የሚያስቡ ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ይህን ስል ደግሞ ሕገመንግሥታችንን ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ የእኔ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለዘመናት የተገነባና የተገመደ ውሕድ ማንነት ነው፡፡ ይኼ ውሕድ ማንነት የተገነባው ማንኛውም በዓለማችን ላይ የሚኖሩ ሀገሮች እንዳደረጉት ሁሉ በተለያዩ ዘመናት የተደረጉ ጦርነቶች፣ በአራቱም አቅጣጫ ይደረጉ የነበሩ የንግድ ልውውጦች፣ የሕዝቦች ዝውውርና ፍልሰትን የመሳሰሉት ነገሮች በመደመር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ነው ኢትዮጵያዊ የሚባል የተለየ አስተሳሰብ፣ የተለየ ዝንባሌና መሰል ገፅታዎችን የፈጠረው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት የተለያዩ ሕብረ ባሕል፣ ቋንቋ እና ለዘመናት በዘለቀ ማኅበራዊ ሥልጣኔ የተነባ ማንነት ነው፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ምን ምን ናቸው?

ዮሐንስ፡- ኢትዮጵያዊ እሴት ስንል ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር አብረን በቆየንባቸው ዘመናትና በሀገረ መንግሥት ግንባታው ውስጥ እንደተሳተፍን ሕዝቦች ለዘመናት ያዳበርናቸው በርካታ እሴቶች አሉን፡፡ ቅድመ ታሪካችን እንደሚታወቀው በአክሱም፣ በላሊበላ፣ በጎንደርና በሌሎችም ቦታዎች የራሱን የሥልጣኔ አሻራዎች እያሳረፈ አልፏል፡፡ በየትኛውም ባሕልና ቋንቋ ውስጥ ያሉ የሀገራችን ሕዝቦች አጉልተው የሚያይዋቸው እሴቶች የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሌላው ዓለም የሚታየው ግላዊነት ነው፡፡ እኛ ሀገር ግን አንድ ሰው ብቻውን አይቆምም፡፡ በጣም የጠለቀ ማኅበራዊ ትስስር አለን፡፡ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍላችን ዘንድ ከልደት እስከ ሞት ድረስ ማኅበራዊ አጀባ አለ፡፡ በውልደት ቀን ጎረቤት ተሰብስበው ደስታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በሕመም ጊዜ ተሰብስበው ያስታምማሉ፤ በሞት ጊዜም ተሰብስበው ይቀበራሉ፤ ይህ ጠንካራ የኾነ ማኅበረሰባዊ ትስስራችንን ያሳያል፡፡ ደቦው፣ እድሩ፣ እቁቡ ሁሉ እዚህ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአትንኩኝ ባይነት፣ የአልበገርም ባይነት እና ውርደትን አለመቀበልም ሌላኛው የእሴታችን አካል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ እራሱን ለባርነት አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ይኼ ትልቁ በኢትዮጵያዊነታችን ያዳበርነው እሴት ነው፡፡

ግዮን፡- ይህ ትውልድና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል? ተግዳሮት የሚባሉት ነጥቦችስ ምን ምን ናቸው?

ዮሐንስ፡- ትውልዱና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል በሚለው ሀሳብ አልስማማም፡፡ ነገር ግን ትውልዱና ኢትዮጵያዊነት እንዲለያዩ ተሞክሯል የሚለው ትርክት ይስማማኛል፡፡ በተለይ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ሺ ዘመናት ተሻግሮ የመጣ እሴታችን ተሸርሽሮ ባዕድ የፖለቲካ አስተሳሰብና እስከዛሬም ድረስ ያልፈተናቸውን ችግሮች አሸክሞን አልፏል፡፡ በጋራ እሴታችን ላይ አንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለማቆም ማንኛውም ሰው በዚህች ሉዓላዊት ሀገር ላይ እኩል መብት ሊከበርለት፣ ፍላጎቱን በአደባባይ እኩል መግልፅ ሊችል፣ እኩል የሥልጣን ዕድል ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄ ማንኛውም የሠለጠነው ዓለም እያደረገው ያለ ነገር ነው፡፡ በሀገራችንም ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን አንስቶ በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለ ጥያቄ ነው፡፡ ይሄን የሕዝቦችን የፍትሕ፣ የዴሞክራሲና የእኩልነት ጥያቄ የ1966ቱም የ1983ቱም አብዮትና የመንግሥት ለውጥ  ሳይመልሰው እስከአሁንም የቀጠለ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የመጡ ባዕድ አስተሳሰቦች የእነሌሊንና የእነእስታሊን እሳቤዎች በርዘውናል፡፡ ይሄ ደግሞ ተግዳሮታችን ነው፡፡

ነገር ግን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የባዕዳን ትምህርት ዘንቦብን፣ የመለያየት፣ የመከፋፈልና የመላላት መከራን ተቋቁመን እንደ ሀገር አብረን መቆም ችለናል፡፡ ይሄ ደግሞ ትውልዱና ኢትዮጵያዊነት አለመነጣጠላቸውን ያሳያል፡፡ በእርግጥ የውጭም የውስጥም ኃይሎች ትውልዱን ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል ሠርተዋል፡፡ ለምሳሌ የውጭ ኃይሎች ምሥራቅ አፍሪካን ለመከፋፈልና ጂኦፖለቲካውን ለመቆጣጠር ሠርተውብናል፡፡ ብዙዎቻችን እንደምረዳው ዘጠና ከመቶ የሚኾነው የዓለማችን ንግድ የሚተላለፈው በበራችን ላይ በቀይ ባሕር ነው፡፡ በተጨማሪም በገነባነው የነጭ የበላይነትን የማይቀበል አስተሳሰብ ስብዕናና መሠል ነገሮች እራሳችንን እንዳንችል አበክረው ጥረዋል፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ ተቋቁመን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ ትውልዱና ኢትዮጵያዊነት አልተለያዩም፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው ግብር?

ዮሐንስ፡- ስሜትና ግብር ተለያይተው የሚቆሙ ነገሮች አይደሉም፡፡ በእኔ እይታ ስሜትና ግብር ነፍስና ሥጋ ተደርገው የሚገለጹ ናቸው፡፡ ስሜት የሚታየው ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ የሚነዝረው ነገር ላይ ነው፡፡ ግብር የሚባለው ደግሞ ይህን የስሜት እርሾ ተጠቅሞ አንዲትን ነፍስ ለሀገር ክብር አሳልፎ ለመሥጠት ሲባል የሚደረገው መዋደቅ ነው፡፡ ስሜት የሌለው ግብር ወይም ግብር የሌለው ስሜት ሮቦት ላይ ብቻ የሚገለፅ እንጂ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚሠራ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ስሜትና ተግባር የተቀላቀሉበት ማንነት ነው፡፡

ግዮን፡- ከአካታችነት አንጻር በኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ ይታያሉ የሚባሉ ጉድለቶችን ይቀበላሉ? ከተቀበሉስ እንዴት መሟላት(መዳበር) አለባቸው ይላሉ?

ዮሐንስ፡- እቀበላለሁ፤ የምቀበልበት አግባብ ግን አሁን ላይ የምንሰማው ትርክት ትክክል ነው ብዬ አይደለም፡፡ “አንድ ብሔር፣ አንድ እምነት አንድ ማንነት ተጭኖብን ኖረናል” የሚለውን አስተሳሰብ አላምንበትም፡፡ ነገር ግን በኋላ ቀርነታችን ሳቢያ በርካታ በሀገራችን ያሉ ባሕልና ማንነቶችን በእኩል ደረጃ “አላዳበርናቸውም” የሚለውን ሀሳብ እቀበላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ኾን ተብሎ በአሻጥር “በአንድ ብሔር፣ በአንድ ሃይማኖት፣ በአንድ ባሕልና በአንድ ቋንቋ ተሠርታለች” የሚለውን ትርክት አልቀበልም፡፡ የታሪክ ሂደቱ ግን በሌሎች ሀገሮች እንዲሚታየው በከፊልም ቢኾን ይሄን አምጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የሠዎች የመቀራረብና የሥልጣኔ ውጤት ነው፡፡ ዛሬ በዓለማችን ከ6 ሺህ በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቋንቋዎች ከአንድ ትውልድ በኋላ ወደ 3ሺህ ሊወርዱ ይችላሉ፡፡ ይሄ ሂደት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የሰው ልጅ እየሰለጠነ ሲመጣ የበለጠ ለመግባባት ወደ አንድ ዓይነት ነገር እየተሰበሰበ ይመጣል፡፡

የሰው ልጅ እየተቀራረበ በሄደ ቁጥር እሴት የመጋራት ባሕሪ አለው፡፡ ይሄ ሰብዓዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን እድል ያላገኙ እሴቶች እድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ያ ማለት ግን በግዳጅ መኾን አለበት ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ አሁን ላይ የባሕል ጭቆና አለ ማለት አይደለም፡፡ ትላንትም ኾነ ዛሬ የባሕል ጭቆና ደርሶብናል ብለው የሚያቀነቅኑ ወገኖች ልጆቻቸውን ከራሳቸው ቋንቋና ባሕልም በላይ በአውሮፓ ትምህርት ቤት ነው እያስተማሩ የሚያሳድጉት፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን በጥልቀት ካየነውና ካጠናነው “በብሔሬ ኮታ ሥልጣን ይገባኛል” የሚል ስግብግብነትን የተላበሰ ፖለቲካዊ የሥልጣን ጥያቄ እንጂ የጭቆና ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ ሙሽራ በሰርገኛ እንግዶችና በሚዚዎቹ እንደሚታጀብና እንደሚደምቅ ሁሉ የብሔሮች ቋንቋ፣ ባሕልና ማንነት ኢትዮጵያን ያደምቃታል እንጂ የሕልውናዋ ስጋት አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር የሀገሪቱ መድመቂያ እንጅ የሕልውናዋ ስጋት አይደሉም፡፡ ይኼ ደግሞ አሁን ባለችው ኢትዮጵያዊ ውስጥ እውን የኾነ ጉዳይ ነው ሌላ ትግል አያስፈልገውም፡፡ የትኛውም ጎሳና ብሔረሰብ ልቡ የወደደውን የመልበስና የመጨፈር እንዲሁም የማከናወን መብትን ተጎናጽፏል፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን የደበዘዘ የሚመስል ባለሚናነት እንዴት ወደነበረበት ቁመና መመለስ ይቻላል?

ዮሐንስ፡- አንድ ሀገር የፖለቲካ ልሂቃን ተሰባስበው የሚፈጥሩት ትርክት ውጤት ነው፡፡ እንደዚህ ብለን ካመንን ያለፍናቸው ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ትርክት የሃይማኖት አባቶችን ሚና እንዴት እንደሚያየው ማጤን ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ሥርዓቶች የሀገር ሽማግሌዎችን ሚና የሚያጎሉ ወይስ ተላላኪ አድርገው የሚጠቀሙ ሥርዓቶች ነበሩ የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ ኃይማኖትም ሽማግሌም አልነበረም፡፡ እንደሚታወቀው ደርግ ሥልጣኑን ሲጀምር ሽማግሌዎችን ሰብስቦ በመረሸን ነው፡፡ የሦስቱንም የእምነት አባቶች ረሽኖ ነው ወደ ሥልጣን የተፈናጠጠው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሥርዓት ለሽምግልናም ለሃይማኖትም ክብር ያልነበረው ሥርዓት ነበር፡፡

ከዚህ ሥርዓት በኋላ የመጣው የኢሕአዴግ ሥርዓትም ሽማግሌና የእምነት አባት እንዳይኖር ካድሬና ተላላኪ በማድረግ አደብዝዞ ጥቅመኛ ሥርዓትን ገነባ፡፡ ስለዚህ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በሀገራችን የሞራል እሴታችን ተሠብሯል፡፡ የሚከበር ሽማግሌ፤ የሚፈራ የሃይማኖት አባት እንዳይኖረን ተደርጓል፡፡ ይሄን ተከትሎ ነው ግብረ ገብነት የጎደላቸው የመንጋ ፍርዶች በየአካባቢው የተፈፀሙት፡፡ ስለዚህ ይህን የወደቀውን የሞራል ስብዕና ለማንሳት ሃይማኖት ለሃይማኖት አባቶች፤ ሽማግልናን ለአሸማጋዮች መተው ይኖርብናል፡፡ ሽማግሌዎች እንደባሕሉና እንደወጉ ሽምግልናቸውን እንዲያከናውኑ ከካድሬ ሰንሰለት ነፃ ልናደርጋቸው ይገባል፡፡

ግዮን፡- ማኅበራዊ ድረገፆች ለኢትዮጵያዊነት ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወቱ ምን ዐይነት አዳዲስ ስልቶች መነደፍ ይኖርባቸዋል?

ዮሐንስ፡- ማኅበራዊ ሚዲያ ዋነኛ መሠረቱ ሞራል ነው፡፡ ለእውነትና ለፍትሕ በመቆምና “እውነት ያልኾነን ነገር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አልፅፍም” የሚል ሞራል በውስጣችን ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ማኅበራዊ ሚዲያ ሁለት ሕጎች ያስፈልጉታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኸውም የተፃፈ ሕግና የሞራል ሕግ ነው፡፡ ዜጎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያልተገባ ነገር ሲያደርጉ የሕግም ተጠያቂ ሊኾኑ ይገባል፡፡ ሕዝብና ሕዝብን የሚያጣላ፣ ሀገራዊ እሴትን የሚንድ፣ እንደ ማኅበረሰብ እንደርስበታለን ብለን የምናስበውን ነገር የሚያስተጓጉል ነገር የሚለጥፍ አካል በሕግ አግባብ ተጠያቂ መኾን አለበት፡፡ በሌላ በኩል በሞራል ሕግም መታየትም አለበት፡፡ የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ኾኜ ሞራል የጎደለው ጽሑፍ ስጽፍ የዕምነት ተጋሪዎቼ ሊወቅሱኝና ሊያርሙኝ ይገባል፡፡ ማኅበረሰቡም ሊገስጸን ይገባል፡፡ ስለዚህ መደረግ ያለበት በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ያላቸው አንቂዎች “ደስ ያላቸውን ሃሳብ ይጻፉ” ተብለው ከሚተው ሰብሰብ ተደርገው የውይይት መድረክ ሊዘጋጅላቸው ይገባል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያን ማንም ሰው የፈለገውን እንዲጽፍ መፍቀድ ለአንድ ሕፃን ልጅ ሽጉጥ አቀባብሎ እንደመስጠት የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ለሀገርና ለማኅበረሰብ እንዲጠቅም አድርጎ በኃላፊነት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ተጠያቂነት ያለው አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

ግዮን፡- ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነት ይዞ እንዲቀጥል ከሕግ፣ ከመዋቅርና ከሥርዓተ ትምህርት አኳያ መስተካከል አለባቸው የሚሏቸው ነጥቦች ምን ምን ናቸው?

ዮሐንስ፡- እንደሚታወቀው አሁን ላይ ሥርዓተ ትምህርቱ ተከልሶ ሙከራ ተጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ላይ በርካታ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥናት ካካሄዱ ሰዎች ደግሞ በግሌ እጅግ የማደንቃቸውና ዛሬ በሕይወት የሌሉት ዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” የሚል ጥናትና ምርምር ሠርተዋል፡፡ በጥናታቸው የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ዋነኛው ችግር ትምህርቱ የተቀረጸው በነጮች እሴት ላይ መኾኑን ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ ቀደም ባለው ጊዜ ቅኔ እንደሚችል የተጠየቀ ሰው በተግባር ይቀኛል፡፡ ዛሬ ላይ ግን “ቅኔ ትችላለህ?” ተብሎ የተጠየቀ ሰው “paper” ሠርቶ ነው የሚያቀርበው፡፡ ትውልዱ አሁን ላይ ቅኔ ወይም ተረት ቢባል በእነአርስቶትልና ፕላቶ ንድፈ ሀሳብ የታጀበ ጥናት ነው የሚያቀርበው፡፡ ስለዚህ የራሳችን እሴት ላይ የተመሠረት ተግባራዊ የኾነ ትምህርት ላይ መመለስ ይኖርበናል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ሥርዓተ ትምህርታችን የተከለሰ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማኅበረሰቡ ትውልዱን በመልካም ሥነምግባር መቅረፅ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ከሕግ አንፃርም በሕግ ማዕቀፍ ዙሪያም የወጣቶችን ስሜትና መረዳት ግምት ውስጥ ያስገባ ሕግ መቅረፅ ያስፈልጋል፡፡ በእርምት እርምጃም ወጣቶች ከባሕሪያቸው የሚስተካከሉበት የማረሚያ ሥርዓት ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

ግዮን፡- የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ካላቸው ጥብቅ ትስስር አንጻር ዜጎች እንዲያውቋቸው፣ በዓለምም ይበልጥ እንዲታወቁና እንዲጠበቁ ምን ይደረግ ይላሉ? ሓላፊነቱንስ የማን ነው?

ዮሐንስ፡- በመጀመሪያ ደረጃ መታረም ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ላሊበላ የአማራ አይደለም፤ አክሱም የትግሬ አይደለም፤ ሶፍዑመር የኦሮሞ አይደለም፤ ሁሉም የጋራ የኢትዮጵያውያን ቅርሶች ናቸው፡፡ ቅርሶችን በየብሔሩ መከፋፈል ትክክል አይደለም፡፡ ያቆየናቸውን ሀገራዊ እሴቶች በብሔር መከፋፈል የለብንም፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ብቻ ተለይቶ የገነባት ከተማና ሀገር፤ ወይም የሚቆይ ቅርስ የለም፡፡ ሀገር የምትገነባው በሁሉም ሕዝብ ተሳትፎ ነው፡፡ ስለዚህ አገሪቱ ውስጥ ያለው ሀብት ሁሉ የሁሉም ነው የሚለውን ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህም በሥርዓተ ትምህርታችን፣ በመዝሙሮቻችን፣ በሥነ ቃላችን፣ ለልጆች በምናዘጋጃቸው ልዩ ልዩ መጫዎቻዎች ውስጥ እያካተትን ትውልዱ የእርሱ እንደኾነ እንዲገባው ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ግዮን፡- አባቶቻችን ለዚህ አገር በክብር መቆየት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለተከታዩ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ትውልድስ ለቀጣዩ ለማስተላለፍ ምን ይጠበቅበታል? ምን ያድርግ? ዮሐንስ፡- የአክሱም ሥልጣኔን የተቀበሉ ቀደምቶቻችን ላሊበላን ጨምረው ነው ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላለፉት፡፡ ላሊበላና አክሱምን የተቀበለው ትውልድ የጎንደር ቤተመንግሥትን ጨምሮ ነው ለተከታይ ያስተላለፈው፡፡ በኋላ የመጣው ትውልድም የራሱን የየዘመኑን አሻራ እየጨመረ ነው እዚህ ያደረሰው፡፡ ስለዚህ እኛም የነበረውን እያከበርን የየዘመናችንን እየሠራን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ የዚህ ትውልድ ዋና ኃላፊነት የጀመራቸውን ሀገራዊ ሥራዎች እውን ማድረግ ነው፡፡ እኔ የሚያሳስበኝ በዘመናችን የምንሠራቸው ድልድዮች፣ ግድቦች እና የመሳሰሉት ነገሮች አይደሉም፡፡ እኔ የሚያሳስበኝ የተበላሸ ማኅበራዊ ስምምነታችንና ፖለቲካችን ላይ ያለው መግባባት ነው፡፡ ይሄ ማኅበራዊ ስምምነትም ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ላይ እኩል መብት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥርዓት ላይ ማተኮር ነው፡፡ ስለዚህ ይኸ ትውልድ ሀገራዊ ስምምነትና እርቅ ፈጥሮ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የመጣንበትን የተበላሸ መንገድ አርሞ ማለፍ ይኖርበታል፡፡ ኃላፊነቱም ይኸው ነው፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...