ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት?

Date:

ብዙዎች ኢትዮጵያና ኤርትራ በቀጣይ ሊገቡ የሚችሉበት ጦርነትን ተከትሎ ከጀርባቸው ሊሰለፉ የሚችሉ ኃይሎች እነማን ሊኾኑ ይችላሉ የሚለው ጥያቄም ጎላ ብሎ መታየት ይኖርበታል እንደማለት ነው፡፡

በተጨባጭ እንደሚታየው ኤርትራ በቀይ ባሕር ክልል ወሣኝ መልክአምድር ላይ የተሰየመች ሀገር ብትኾንም፣ የትንሽዋ ጂቡቲን ሲሶ ያህል እንኳን የዓለም አቀፍ ኃያላን የጦር ቤዛቸውን የመሠረቱባት ሀገር አለመኾንዋ ነው፡፡ እንግዲህ በኤርትራ በአሁኑ ወቅት አንድም የዓለም ኃያል መንግሥት ወታደራዊ የጦር ሰፈር የሌለው መኾኑ ብቻውን ኢትዮጵያን የልብ ልብ እንዲሰማት ያደርጋል፡፡ ይኽን የሚያስብለው አንድ ኃያል ሀገር በሌላ ሀገር ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለመገንባት ስምምነት ላይ ሲደርስ ምናልባትም ከስምምነቶቹ አንቀጾች መካከል አንዱ፣ የሀገሪቱ መንግሥትን ሕልውና ሊጎዳ የሚችል ማንኛውም አደጋ ሲያጋጥም የመከላከል ግዴታን ሊያስቀምጥ የሚችልበት ዕድል በመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ ልክ በጂቡቲ ፈረንሳይ እንዳለባት ኃላፊነት ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡

ይኽም ኾኖ ግን የዓለም ኃያላን ኤርትራ ውስጥ የጦር መንደር የመገንባት ፍላጎት የላቸውም ፤ አልያም ሙከራዎች አላደረጉም ማለት አይደለም፡፡ በተለይም የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ፣ በፖርት ሱዳን ወታደራዊ ቤዝ የመገንባት ዕቅዷ የተጨናገፈባት ሩሲያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ አሥመራ በተደጋጋሚ ተመላልለች፡፡ የኤርትራ መንግሥትንም እንደ ቁልፍ የአካባቢው አጋር መንግሥት በመቁጠር ብቻ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ደጋግማ ወደ ሞስኮ ጋብዛለች፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስም፣ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ በተባበሩት መንግሥታት ሩሲያ ላይ በተደረሰው ማዕቀብ ብቸኛው ከክሬሚሊን ጎን የቆሙ የዓለማችን መሪ መኾናቸውን አስመስክረዋል፡፡

‹‹ሩሲያ የምትዋጋው ከዩክሬን ሳይኾን ከኔቶ ነው›› በሚለውና ፑቲን ፊት ለፊት ተቀምጠው ባሰሙት ዲስኩር የሚታወቁት ኢሳያስ ግን፣ እጅግ ፈጣን ተላውጦዎችን በሚያስተናግደው የዓለም ፖለቲካዊ ሁኔታ ምክንያት ሩሲያ የፈቀዱላትን የጦር ቤዝ እስካሁን በምድራቸው ሳትገነባ ቆይታለች፡፡ ይባስ ብሎ አሁን ደግሞ በሱዳን የጀነራል አል አልቡርሃን ጦር ድል አድራጊ መኾን፣ በአሜሪካም በትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣት ምክንያት የዋሽንግተንና ሞስኮ ግንኙነት ሌላ ቅርጽ መያዝ ተስፋቸው ላይ ውሃ ሳይቸልስ እንደማይቀር ይገመታል፡፡

ከሩሲያ በሻገር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ አሥመራ መለስ ቀለስ ማለት ያበዛችው ሌላኛዋ ኃያል ሀገር ቻይና ብትኾንም፣ የቤጂንግ የጦር መንደር ግንባታ ጅቡቲ ላይ ሥሙር መኾኑን ተከትሎ፣ ኤርትራ ላይ ያላት ፍላጎት የከበሩ ማዕድናት በማውጣት ላይ ብቻ የተገደበ ኾኗል፡፡ ከዚህ አንጻር ስንመለከተው የኤርትራ መንግሥት ወታደራዊና የደህንነት አጋር ሊኾኑ የሚችሉት መንግሥታት እነማን ናቸው የሚለው ጥያቄ ከሁለት ሀገራት ከፍ የማይል ኾኖ ነው የምናገኘው፡፡ እነርሱም ሳዑዲ ዐረቢያና ግብጽ ናቸው፡፡

ሳዑዲ በርግጥም የኤርትራ ታሪካዊ ወዳጅ ከመኾኗ በላይ፣ ከተባበሩት ዐረብ ኤመሬቶች ጋር ያለባት ውጥረት አሥመራ ከአዲስ አበባ ጋር በምትገባበት ማንኛውም ጦርነት ኢሳያስን ከጀርባ ልትደግፍ እንደምትችል ይገመታል፡፡ ሳዑዲ ከዓመታት በፊት በየመን በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት በእጅ አዙር ከተባበሩት ኤመሬትስ ጋር መታኮሷንና፣ አሁን ላይ ኤመሬትስ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ወዳጅ መኾኗን በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ክልል እንድትገለልና ‹‹ሻዕቢያን›› ጨምሮ የተለያዩ ተገንጣይ ኃይሎች እንዲደራጁ በማገዝ ረገድ ያላት ድርሻ ትልቅ መኾን፣ በኢሳያስ መንግሥት ላይ ከኢትዮጵያ በኩል የሚቃጣ ማንኛውንም አደጋ አብራ ከመመከት ወደኋላ ላትል ትችላለች የሚለውን መላምት ለእውነት ያቀርበዋል፡፡ ሳዑዲ ከኤመሬትስ ጋር ባትወዳደርም የተለያዩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን) ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሣርያዎችን የታጠቀች ሀገር ከመኾኗ አንጻርም፣ ለኤርትራ የሚኖራት የጦር መሣርያ ድጋፍ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረውን ውጊያ ቀላል ላያደርገው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

***

በሌላ በኩል የአሥመራ ወታደራዊ አጋር መኾኗን በፊርማዋ ጭምር ከወራት በፊት ያረጋገጠችው ግብጽ ደግሞ በቀጥታ ወታደሮቿን አስገብታ ጭምር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖራት ግጭት ተሳታፊ ልትኾን ትችላለች፡፡ ይኽ ዛሬ ሳይኾን ገና ከዐሥራ አምስት ዓመታት በፊት ግሪጎሪይ ኮፕሌይ የተባለ ጋዜጠኛ ‹‹ኢትዮጵያ ዳግም ወደቀይ ባሕር እንዳትመለስ ካይሮ ቀይ ደሟን ከኤርትራ ጋር ከማፍሰስ አታመነታም›› በማለት መጻፉ አስረጂ ይኾናል፡፡

እዚህ ላይ ግብጽን አስመልክቶ የሚነሳው ችግር ‹‹ወቅቱ›› ነው፡፡ ምናልባትም ኢትዮጵያ ይኽን ወቅት ኤርትራ ላይ የቃላት ፍላጻ ለመወርወር ለምን መረጠችው በሚለው ጥያቄ ውስጥ ወሣኝ መልስ የምናገኘውም እዚህ ጋር ነው፡፡ ዓለም በግልጽ እየታዘበ እንደሚገኘው የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ጡዘት ግብጽንና እሥራኤልን ወደማፋጠጥ ደረጃ ተሻግሯል፡፡ ይኼ ደግሞ ሀገራቱን በቀጣይ የለየለት ጦርነት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ለእርግጠኝነት የቀረቡ ትንበያዎች እየተነገሩበት ነው፡፡ በሀገራቱ ባለሥልጣናት ዘንድም ይኽ ጉምጉምታ በግልጽ መሠማት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ይኽ እውነታ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ቢገቡ፣ ካይሮ በአሥመራ በሚኖራት ወታደራዊም ይኹን ፖለቲካዊ ሚና ውስጥ መሳሳትን ይፈጥራል ብለው የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ የግብጽ ከእሥራኤል ጋር የምር ግጭት ውስጥ መግባት አይቀሬ ከኾነም፣ ካይሮ በማንኛውም አካባቢ በሚኖራት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የእሥራኤልን ከተቃራኒው ኃይል ጎን የሰለፍ ዕድል በዛው ልክ ያሰፋዋል እንደማለት ነው፡፡ በዐጭር ዐማርኛ እሥራኤል ወይም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጎን የሚሰለፉበት እውነታ ግልጽ ኾኖ ይመጣል እንደማለት ነው፡፡ እሥራኤል ከዚህ ቀደምም ግብጽ ሞቃዲሾ ድረስ ዘልቃ ጸረ ኢትዮጵያ ጥምረት ለመፍጠር በምትሞክርበት ወቅት፣ ከሶማሊላንድ መንግሥት ጋር ተነጋግራ ከኤመሬትስ ቀጥሎ ወታደራዊ ቤዝ ለመገንባት ስምምነት ላይ የደረሰች ሀገር መኾን ችላ እንደነበር ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡

ያ ስምምነት በኤመሬቶች አግባቢነት የተፈረመ ከመኾኑ አንጻር፣ ኤመሬትስ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁልፍ የኢኮኖሚና የደህንነት አጋር ከመኾኗ አንጻር ከተቃኘ፣ ካይሮ ከቴል አቪቭ ጋር ያልተቋጨ ጉዳይ እስካላት ድረስ በኤርትራ የሚኖራት ተሳትፎ ጉዳዩን ወደ እጅ አዙር ጦርነት ሊወስድ የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ሲኾን፣ ግብጽ ኤርትራን ለቀቅ አድርጋ ‹‹ሥራሽ ያውጣሽ›› ማለትን ልትመርጥ ትችላለች፡፡

ይኽ ሲኾን ምናልባትም የኤርትራ የመጨረሻ ተማጽኖ ወደ ሩሲያ ሊኾን ይችላል፡፡ አሥመራ ለሞስኮ በብቸኝነት ሽንጧን ገትራ ዓለም ፊት ያሳየችውን ውግንና እንደ ውለታ በማስታወስ ፕሬዝዳንት ፑቲን ከጎኗ እንዲቆም መለማመን ውስጥ ልትገባ ትችላለች፡፡ ጥያቄው ግን ፑቲን የኤርትራን የክፉ ቀን ውለታ ለመመለስ ‹‹ምቹ ወቅት ላይ ነው ወይ?›› የሚለው ነው፡፡ አሜሪካና ሩሲያ አሁን ላይ ከጀመሩት በጎ የመቀራረብ ምልክቶች አንጻር፣ በቀጣይ ሞስኮ ላይ ተጥለው የነበሩት የነዳጅና የንግድ ማዕቀቦች የሚነሱበት እውነታ የሚፈጠር ከኾነ፣ ሩሲያ ለኤርትራ ከንፈሯን ከመምጠጥ ውጪ ሌላ የምታደርግላት ነገር ሊኖር አይችልም፡፡

ይኹን እንጂ የፑቲንና ትራምፕ ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያድግበት ተጨባጭ ሁኔታ በመሬት ላይ የማይፈጠር እስከኾነ ድረስ እስካሁን በአፍሪቃ ቀንድ ምንም ዐይነት ወታደራዊ ቤዝ የሌላት ሩሲያ ኤርትራን በዋዛ ላትለቅ የምትችልት ምክንያት ይኖራታል፡፡ የዓለም ኃይል አሰላለፍ ሁኔታ ግን ከሁለተኛው ይልቅ ለመጀመሪያው ነጥብ የሚያጋድል ይመሥላል፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 223 የካቲት 29 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በፖለቲካዊ ሳይሆን በቴክኒካዊ መንገድ መፈታት አለበት

በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ፣ እና የመካከለኛው ምስራቅ...

የ7 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አለመከናወኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሚተዳደሩ 7 የጋራ መኖሪያ...

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በ80 ዓመታቸው ከዚህ...