ኢኩዊቲ ባንክ፣ በምስራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም ከሚባሉ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ የሆነው፣ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ። ይህንን ፍላጎት አስመልክቶ ባንኩ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ዉይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ባንኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየቱን አድንቀዋል። አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉ፣ ሀገሪቱን በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ተመራጭ መድረክ እንዳደረጋት ገልጸዋል።
ኮሚሽኑም ለባንኩ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢኩዊቲ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀምስ ምዋናጊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባንኩ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለመግባት ሲያቅድ እንደነበረ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ መከፈት ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው የገለጹት ጀምስ፣ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ለሌሎች የውጭ ኩባንያዎች ምሳሌ መሆን እንደሚፈልግ አስረድተዋል።
ኢኩዊቲ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤቱ በናይሮቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በሩዋንዳ፣ በደቡብ ሱዳንና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰፊ የሥራ ልምድ ያለው ተቋም ነው።
ባንኩ በኢትዮጵያ ተወካይ ቢሮ ያለው ሲሆን፣ በ1984 ዓ.ም ከተመሠረተ በኋላ ሁሉን ያካተተ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል። በናይሮቢ የአክሲዮን ገበያ ላይ በይፋ የተመዘገበ የመጀመሪያው የጥቃቅን የፋይናንስ ተቋምም ነው።
CapitalNews
