የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ሥራ ኮሚሽን በከተማዋ የሚገኙ ከ1 ሺህ 100 በላይ የቁጠባና ብድር ማኅበራትን በማዋሃድ የፋይናንስና የብድር አቅማቸውን ለማጠናከር እንዲሁም በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየሠራ መሆኑን ገለጸ።
የኮሚሽኑ የፋይናንስ ህብረት ሥራ ልማት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አክሊሉ፣ ማኅበራቱን ከማብዛት ይልቅ ውስንና ጠንካራ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ በማዋሃድ የተሻለ የፋይናንስ አቅምና የብድር አቅርቦት እንዲኖራቸው እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማኅበራቱ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አንጻር ወደኋላ የቀሩ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ይህንን ክፍተት ለመቅረፍና ማኅበራቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ኮሚሽኑ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ማኅበራቱን ማዋሃድ የብድር አገልግሎትን ከማስፋፋት ባለፈ ለአባላት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡና በዘላቂነት እንዲጠናከሩ ወሳኝ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
