የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ባለው ግጭት በርካታ ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ከሰኔ 2016 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. ያለውን ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ ባለ 152 ገጽ ዓመታዊ ሪፖርት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱም በሕይወት የመኖር መብት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶች በርካታ ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል።
ሪፖርቱን ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ያቀረቡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎ፤ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ባሉ ግጭቶል ምክንያት ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በክልሉ ያለው ታጣቂ ቡድን እራሱን “ፋኖ” ብሎ የሚጠራው ኃይል ምክንያት በርካታ ንፁሀን ዜጎች መሞታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ኃይሎችና በኦነግ ሸኔ ግጭት ምክንያት በርካታ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ በመንገድ ላይ በርካታ ዜጎች በኦነግ ሸኔ ታግተው ግድያ እንዲሁም መደፈር እንደደረሰባቸው መመላከቱን ኮሚሽነር ብርሀኑ ተናግረዋል።
በዚህም ከኦሮሚያ እና አማራ በተጨማሪ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ቤንሻንጉል እና ጋምቤላ በአጋቾች ምክንያት ዜጎች የግድያና የመደፈር አደጋ እንደደረሰባቸዉ በሪፖርቱ ቀርቧል።
በአማራ ክልል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ቀድሞ የተነሳ ቢሆንም፤ በክልሉ አሁንም በርካቶች በጅምላ እንደሚታሰሩ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ “ይህ ድርጊት በኦሮሚያም ክልል በተመሳሳይ ተባብሶ የቀጠለ ነው” ብለዋል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ የምክረ ሀሳቦችን ያቀረበ ሲሆን፤ በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጩ መንግሥትን ጨምሮ ቁርጠኛ እንዲሆን አሳስቧል።