ሠሎሞን ለማ ገመቹ
ስለ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መልካም ሥራና ስለ ደካማ ጎናቸው ለመፃፍ የደፈሩት አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ‹‹ክፉ ልማድ መልካም መስሎ ይኖራል፡፡ ደግ ነገር መምከር መደገፍ ነው እንጂ መድፈር አይባልም›› ብለው ነበር፡፡ እኔም ስለ አንዳንድ እየበረቱ ስለመጡ፣ በትዕግስት ሲታለፉ እንደ ፍርሃትና እንደ አለማወቅ ተቆጥረው መንሰራፋት ስላበዙ ጉዳዮች የበኩሌን ለማለት ጣቶቼን ከኮምፒውተሬ ቁልፎች ጋር አስማማሁ፡፡ መደፈር አይገባቸውም ነበር… የሚባሉትን ወገኖች ለመድፈር ሳይሆን ደግ ነው ያልኩትን ምክር ለመሰንዘርና መልካም እየመሰለ የኖረውን ‹‹ክፉ ልማድ›› ለመንቀፍ ስልም ‹‹የመቃብሩ በጎች›› በሚለው ርዕስ የሚከተለውን ወግ ይዤ ቀረብኩ፡፡
በመሠረቱ ይህ ርዕስ ዝም ብሎ በማራኪ ርዕስነቱ የተመረጠ አይደለም፡፡ ከመቆጨትና ከመብሰልሰል የስሜት ማሕፀን በሞራላዊ ምጥ የተወለደ ነው፡፡ ደግሞም በቀጥታ ‹‹የመቃብሩ በጎች የትኞቹ ናቸው?›› ወይም ‹‹የመቃብሩ በጎች ሲባል ምን ለማለት ተፈልጎ ነው?…›› የሚለውንና መሰል ጥያቄዎችን እንዲያጭር ተብሎ በደፈናው የቀረበ ርዕስ አይደለም፡፡ ይልቁንም በርዕሱና ርዕሱን መነሻ ባደረገው ወግ አማካይነት አማኙ ማኅበረሰብ ወይም ምዕመን ሰፋ ያለ ውይይት እንዲያደርግበትና በሚቻለው አቅም የመፍትኄ ሐሣብ እንዲያቀርብብበት የሚጋብዝ ርዕስ ነው፡፡ በተጓዳኝም የመቃብሩ በጎች የማን ናቸው? ማንስ ነበር ጠባቂያቸው? እነዛንስ በጎች ማን በላቸው?… ለሚሉት ጥያቄዎች አጠር ያለ መልስ ከምጥን ማብራሪያ ጋር ለማቅረብ እንዲያመች ተደርጎ የተመረጠ ርዕስ ነው፡፡
እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የመቃብር ሥፍራዎች ከቤተ-ዕምነት ጀርባ፣ አጠገብ፣ በከፊል ዙሪያውን፣ በቤተ-ዕምነቱ አቅራቢያ ይገኛሉ፡፡ ቤተ-ዕምነቶች ደብሮችም ይሁኑ መስጅዶች ወይም የዘመኑት የጸሎት ቤቶች ደግሞ፤ የምዕመናን፣ የኃይማኖት አባቶችና ሊቃውንቶች… ሁነኛ ማዕከላት ናቸው፡፡ ፍጡራን ከፈጣሪያቸው ጋር በአርምሞ… ‹‹ይነጋገሩባቸዋል›› ወይም በጸሎት/ በዱዓ ‹‹ይገናኙባቸዋል›› ተብለው በሰው ልጆች ዘንድ ሞራላዊ ወይም ማኅበራዊ ተቀባይነትን ያገኙ፣ ሞገስ ያላቸው፣ የተከበሩ ቅዱሳን ሥፍራዎች ናቸው፡፡ በማዕከላቱ ወይም በቅዱሳን ሥፍራዎቹ የሚታደሙትና የሚመላለሱት ግን እንደ ባሕሪያዊ ምሳሌው በጎች፣ ዕርግቦችና ፍየሎች ብቻ አይሉም፡፡ ቀበሮዎች፣ ዕባቦችና ተኩላዎችም እንጂ፡፡
በየቤተ-ዕምነቱ ሥፍራና ማዕከል፤ ተስፋ፣ ቅንነት፣ የዋህነት፣ በጎነት፣ ትጋትና ጨዋነት፣ ቸርነትና ርኅራሄ፣ መረጋጋትና መጽናናት፣ በረከትና ጸጋ… አለ፡፡ ሆኖም ግን ማዕከሉና ሥፍራው የሰውን ልጅ ህሊና ወይም መንፈስ የሚያለመልም ቅዱስ ስብከት የሚሰበክበት የመሆኑን ያህል፤ በተቃራኒ የሆነው ቃልና ድርጊት የሚደመጥበትም፣ የሚስተዋልበትም የመሆኑን ሐቅ ማስተባበል ወይም ፈፅሞ መካድ አይቻልም፡፡ ለአብነት ያህል ቀበሮዎቹና ተኩላዎቹ የበግ ለምድ ለብሰው በግልጽ የሚታዩት፤ በነዚያው ምዕመኑ የተስፋ፣ የመጽናናት፣ የርኅራኄ፣ የመልካምነትና በበጎነት የመጽናት ትሩፋትን ቃሎች ከነትርጓሜያቸው በሚያደምጥባቸው ቤተ-ዕምነቶችና በዙሪያቸው ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ወይም በዚያኛው ሳንል ጥቂት በማይባሉት ቤተ-ዕምነቶች የበግ ለምድ ለብሰው ብቅ ጥልቅ የሚሉት ቀበሮዎችና ተኩላዎች እጅግ በጣም ፈጣጦችና ከናካቴውም ይሉኝታ የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ናቸው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን መፍራት›› የሚለውን ቃል በራሳቸው ለራሳቸው ‹‹ፈጣሪን መድፈርና መጋፈጥ›› ወደሚለው የለወጡት ይመስላሉ፡፡ በደፋር ቃላቸውም ይሁን በአፈጠጠና በአገጠጠ ነውረኛ ተግባራቸው ቅንጣት የመደናገጥ ስሜት ሳይነበብባቸው፤ በየቅዱሳን መድረኩ ‹‹እናስተምረዋለን! እንመክረዋለን! እንገሥጸዋለን!›› የሚሉትን ምዕመን ደጋግመው ለመሸንገልና ለማታለል ሞክረዋል፡፡ የግራ ቀኙን ኃይማኖታዊ መሰል ጥቅስ እየጠቀሱ ማጭበርበርም ዓይተኛ መለያቸው መሆኑን በገሃድ አሳይተዋል፡፡ ዝርፊያና ቅሚያቸው መልካም መስሎ እንዲቀጥል ያላቸው የማይሰክን ፍላጎትም፤ የምዕመኑን ቁጣ ቀስቅሶ የኃፍረትን ጽዋ እንዲጎነጩ… እስኪያደርጋቸው ድረስ በዕብሪትና በንቀት ብዙ ርምጃዎችን ተራምደዋል፡፡
ምዕመናን ለየኃይማኖታቸው ባላቸው ቀናዒነት… ሲሉ በሚያሳዩት ጨዋነት፣ አስተዋይነትና ትዕግስት የተመላበት የተገባ ተግባር መጋረጃ ውስጥ በመሸሸግ መልካም መስሎ እንዲኖር የሚሹትን ክፉ ልማዳቸውን እንደ ጌጥ በመቁጠር የሚኮፈሱበት ስም የኃይማኖት አባቶችና የቤተ-ዕምነት አስተዳዳሪዎች ቁጥራቸውም ይሁን ዕኩይ ተግባራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እነሱ እንደ ዘመኑ የአውሮፓ የእግር ኳስ ተጫዋች በችሎታቸው የሚፈለጉ ይመስል፤ በድርጊት ተባባሪዎቻቸው አማካይነት ምዕመኑ በቁጣ በተነሳባቸው ጊዜ ከአንደኛው ቤተ-ዕምነት ወደ ሌላኛው ቤተ-ዕምነት የሚዘዋወሩ ናቸው፡፡
ዐመልና ክፉ ልማድ ነውና ከአንደኛው ሥፍራና ማዕከል የተባረሩበትን ተግባር በተዛወሩበትም ቦታ ይደግሙታል፡፡ እንደደረሱ የሤራ ተባባሪዎቻቸውን ይመለምላሉ፡፡ የማይመቻቸውን ይወነጅላሉ፡፡ በሤራ ተባባሪዎቻቸው አማካይነት ጠልፈው ለመጣል ይሞክራሉ፡፡ ለቤተ-ዕምነቱ እና ለምዕመናኑ… ‹‹ይጠቅማል፣ የሚያፀድቅም ነው…›› በሚል መዋጮ ይጠይቃሉ፡፡ የንግድ ቤት እንዲቋቋም ያደርጋሉ፡፡ ያከራያሉ፡፡ ኪራይ ይተምናሉ፡፡ ለከርሳቸው መሙያ… ድግስ ያስደግሳሉ፡፡ ማደሪያቸውን ይከልላሉ፡፡ ምዕመናኑ የየቤተሰቦቻቸውን አስከሬን በሚያሳርፉበት የተከበረ የቀብር ሥፍራ የሚሰማሩት የመቃብሩ በጎች የእነሱ ናቸው፡፡ እንደ በጎቹ ከአራጆቹ ጋር የሚውል ጠባቂም ተመድቦላቸዋል፡፡ የለመለመውን ሣርና ቅጠል… እየበሉ የሰቡት በጎችም፤ ነውርን ጌጣቸው ያደረጉት ሰዎች በከለሉት ማደሪያ ውስጥ በስውር ታርደው፣ በድብቅ ይበላሉ፡፡ በላተኞቹ መቼም የትም… ተድላና ደስታ ገንዘባቸው ነው፡፡
እንዲህ ስለ መሰለውና የኃይማኖትን፣ የአማኞችንና ለመልካም ሥነ-ምግባር ሟች የሆኑ ሰዎችን ሞራል ስለሚነካው ‹‹የመቃብሩ በጎች አርቢዎችና በሊታዎች›› ድርጊት፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ ካለፉት ሃምሳና ስልሳ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን የመጣችበትን መንገድ ጠቋሚ፣ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ወካይ ወይም ገላጭ በሚሆን ደረጃ አሰፋ ጫቦ ምን ነበር ያለው?
‹‹መከባበርን እንደተከለከለ፣ እንደ ሕገ-ወጥ ሸቀጥ ማየት የተጀመረ ይመስላል፡፡ የሌላውን ሰው ስብዕናውን፣ ሐሣቡና ዕምነቱን ለመዘርጠጥ… ለመዝለፍ… መቸኮልና ፈቃደኛ መሆን አለ፡፡ ከአንደበት የሚወጣው ቃል በሌላውም ላይ ሆነ በራስ ላይ ሊተው የሚችለውን በጎም ሆነ መጥፎ ውጤት አለማመዛዘን ብቻ ሳይሆን ላለማመዛዘን መፈለግም ይታያል፡፡ እና ምንድን ነው የሚፈለገው? ምንድንስ ነው የሚያስፈልገው?›› ብሎ ነበር ጋሼ አሰፋ ጫቦ፡፡ ልክ አሁን አሁን በቤተ-ዕምነቶች ጭምር… በአደባባይ በአካል፣ በስውርና በግልጥ ደግሞ በየማኅበራዊ ድረ-ገጹ (ቲዊተሩ፣ ዩ ቲዩቡ፣ ኢንስትግራሙ፣ ሬዲዮ ቴለቪዥኑ፣ ቴሌግራም ፌስ/ፌዝ ቡኩ፣ በየገበያው መሸታ ቤቱ…) እንደምንሰማው፣ እንደምናየው፣ እንደምናነበው ዓይነቱ ጉድ ማለት ነው፡፡
አቤት! አቤት!! አቤት!!!… የክፉ ልማድ አድራጊውና በድርጊቱ የሚመካው ሰው፣ የተንታኙና የዘገባ አቅራቢው ብዛት፡፡ የአዋቂ ነኝ ባዩ መንጋጋት! የሚገርም ነው፡፡ የሚደንቅም ነው፡፡ የሚያታክትና አቅልንም የሚያስት ነው፡፡ የከርሞ ሰዎች ‹‹ሁሉም ከሆነ ቃልቻ፤ ማን ሊሸከም ነው ስልቻ›› ያሉት ወደው አይደለም፡፡ ከፍ ሲል በጥቅስ ስለተቀመጠው ዐመልና ባሕርይ፣ ስለተያያዥ ጥየቄውም ጋሼ አሰፋ ጫቦ፡- ‹‹መቼም የኛ ሰው ችግር፣ የኛ ሃገር ችግር አነሰም በዛ የሚታወቅ ይመስለኛል›› ይለናል፡፡ የሚታወቀው ምንድን ነው? ያው እያንዳንዱ ሰው የሚያውቀውና ‹‹መቼስ ምን ይደረግ?….›› እያለ ሰበብ የሚደረድርበት ነዋ፡፡
ጋሼ አሰፋ ግን ያለው ቃል ላይ አያቆምም፡፡ ‹‹ቢጠና ቢጠና መልሱ አልገኝ ያለው መፍትኄው ነው፡፡ መፍቻ ቁልፉ የጠፋብን ይመስላል›› በማለት ይቀጥላል፡፡ የችግሩ መፍትኄ፣ መልሱ ከወዴት ይገኝ? ለሚለው ጥያቄም እንደ መልስ አድርጎ የሚያስቀምጠው ‹‹አንዱ እንዳይገኝ አድርጎ አስደግሞበት የሰወረው/ የወረወረው ይመስላል፡፡ የድግምትም ሃገር ጭምር ነውና!!›› የሚለውን መላምታዊ ሐሣብ ወይም እያወቅን ያላወቅን መስለን የምንደነጋገር… የምንመስልበትን ወደ እውነተኛ ባሕሪያችን ያጋደለውን ቃል ነው፡፡ ኦ!… ምንድን ነው ‹‹ድግምቱ››? ማንስ ነው ‹‹ያስደገመብን››? ለችግራችን መፍትኄ እንዳናገኝለት አድርጎ፡፡ ራሳችንን መጠየቅ ነው፡፡ በግልም በጋራም፡፡ በየብሔረሰቡም፣ በየፆታውም፣ በየኃይማኖቱም፣ የወል በሆነው ዜግነትም ይሁን አጥር በሚከልለው፣ ጎዳና በሚያጋልጠው መደብም ቢሆን መጠየቅ ነው የሚኖርብን፡፡ ዝም ብሎ ‹‹የትዝታ››ን ‹‹ፈለግ›› ማንበብም ሆነ መከተል ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከነበረው ታሪክና ከዛሬው የተጨበጠ እውነታችን ጋር ድብብቆሽ እንደያዝን መቀጠል አይኖርብንም፡፡ ቁልፉን በራሳችን ላይ ቆልፈን መልሰን ‹‹መክፈቻውን ፈልጉልን›› እያልን መነታረኩ አያዋጣም፡፡ አንዳንድ ምዕመናን ግን ጎበዞች ናቸው፡፡ ያተከኗቸውን የመቃብር ሥፍራ በግ አርቢዎች ወደ አደባባይ ፍርድ ለማቅረብ ጥረዋል፡፡ ቀኙን ለእነሱ ያድርገው፡፡ ብርታቱን ይስጣቸው፡፡ ክቡራንና ክቡራት አንባቢያን፤ ፈጣሪ ያሰንብትልኝ፡፡