ሠሎሞን ለማ ገመቹ.
የሙዚቃ ስበት ፊዚክስ ሊያስተምረን ወይም ሊያስገዝበን እንደሚከጅለው እንደ ነገረ-ማግኔት ሕግ ወይም ቲዎሪ ዓይነት አይደለም፡፡ ስበቱ ሕይወታዊም መንፈሳዊም ጉልበትና ረቂቅነት ያለው ነው፡፡ ሙዚቃ ካልኩትም፣ ከተባለውም በላይ መጢቅና ጥልቅም ነው፡፡ የሙዚቃ ስበት የሚመነጨው ከብዙ የሕይወትና የመንፈስ ተብሰልስሎት ነው፡፡ የሙዚቃ ተብሰልስሎት ስበቱ የመኖር ታምራትና ቅኔ ድምር ውጤት ነው፡፡ ድምር ብቻም አይሆንም፡፡ ብዜት ክፋይ ቅናሽ ነው፡፡ ደግሞም ከዚህም ያለፈ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡
የሙዚቃ ስበቱ ታምራትና ቅኔ ከአንዱ የኑሮ ጥግ ጠርዝ ዕምብርት ቅርንጫፍ ጉጥ… ተነስቶ ወደ ነበረም ይሁን ወዳለ የሚያደርስና የሚመልስ ያው የስሜት ተብሰልስሎት ነው፡፡ ስሜት ደግሞ የአያሌ ነገሮች ድምር ውጤት፣ የልዩ ልዩ ኑሮ መልኮች ቦዲማስ ቀመር ይዘትና ቅርፅ አብነት ነው፡፡ ሙዚቃ በዝማሬ፣ ፍካሬ፣በነሺዳ፣በዕንጉርጉሮ፣በጌሬርሳ፣በሽለላ፣በመንዙማ፣ በቀረርቶ ዘፈን በምንላቸው የድምፅ፣ የስንኝ፣ የዜማ ውኅዶች ውስጥ ከነፍስያ ወደ ጆሮ፣ በጆሮ ወደ ነፍስያ በሚንቆረቆር ድርጊት ሲገለጥ የምናውቀው ዓይነት ቢሆንም፤ የሙዚቃ ስበት ጉዳይ ግን ቅኔነቱም ይሁን ታምራዊነቱ ከመነሻው ጀምሮ ዛሬ እስከ ደረሰበት ዘመንም ይሁን እስከ መፃኢው ጊዜ በሰው ልጅና በተፈጥሮ ትስስር ውስጥ የሚኖረው ሥፍራ አንድም በምሥጢራዊ ገላጭነቱ፣ ሁለትም በስሜታዊ አጥማጅነቱ ሊገደብ የማይችል ሕይወታዊ ቦይ ውስጥ፤ የሰው ልጆችን ከፈቃድ ጋር ጭምር…. በተብሰልስሎት ወላ በትዝታና በናፍቆት፣ በደስታና በፍንደቃ፣ በኃዘንና በሰቀቀን… በሉት ግራና ቀኝ፣ ላይና ታች…የሚጎትት፣ ከፍ ዝቅ የሚያደርግ፣ የሚያዋልል… አይጨበጤ ኃይል ነው፡፡
እስቲ የካሣ ተሰማን የሙዚቃ ስብት አንድ አብነት ወይም ምሣሌ እንውሰድ (የካሣን ተጠቃሽ ሙዚቃ እያደመጡ ቢሆን ይመረጣል)፡-
‹‹ከሰማይ የመጣሽ የእግዚአብሔር ስጦታ
የኑሮ ደጋፊ – የመንፈስ አልኝታ
ሕይወት የምትሰጪ- ሆነሽ መድኃኒት
ሙዚቃ ነሽ ዕኮ – ለሰው አብነት
ብስጭት ጭቅጭቅ – ኃዘን ወይ ትካዜ
ይርቃሉ ከሰው – አንቺ ባለሽ ጊዜ…›› እያለ የሚንፎለፎለው፡፡ እያለ የሚፈሰው፡፡ በስበቱ ግርማና ኃይል ከኑሮ መልክዓ-ምድር፣ ከሕይወት ኩሬ፣ ኃይቅ፣ ውቅያኖስ፣ ከዓለም ዳርቻ…፤ ነፋሱን፣ ወጀቡን፣ ማዕበሉን፣ ነጎድጓዱን፣ ውሽንፍሩን፣ ግለቱን፣ ቅዝቃዜውን፣ ንዳዱን፣ ቆፎኑን… የሚጠራው መልሶም የሚገፈትረው ሙዚቃ ነው፡፡
ስለ ሙዚቃ ስብት ከራሴ ሕይወት ተመክሮ ቅንጣት ምሣሌ ላቅርብ፡፡ ከመወለዴ ከሁለት ነው ከሦስት ዓመት ግድም ቀደም ብሎ፤ ካሣ ተሰማ በመረዋ ድምጡ ያዜመላትን ሙዚቃ ገና ሕፃን ሳለሁ ለማድመጥ ጆሮዎቼ ስል ነበሩ፡፡ በስበቷ ኃይል ተጠምጄ ሙዚቃንና በሙዚቃ የሚተላለፉ ማኅበራዊ መልዕክቶችን ማጣጣም የጀመርኩት ደግሞ በታዳጊነት ዕድሜዬ ነበር፡፡ በዋሽንት፣ በክራርና በመሰንቆ… ምቶች የሚታጀቡ ባሕላዊ ሙዚቃዎቹን እየለየሁ የመወድዱ ልክፍትና ከዚያም ያንኑ መሠረት ያደረገው የስበቱ ኃይል ወደ ጥልቁ የሙዚቃ አፍቃሪነት ውቅያኖስ ውስጥ ወስዶ ዘፈቀኝ፡፡ ‹‹ሞገደኛው! ይህ ኃይለኛው ፍቅሯ ሸብቦ ሸብቦ፤ ከባሕር ላይ ከወቅያኖስ የዘፈቀኝ ስቦ…›› እንዲል ድምጣዊ ነዋይ ደበበ፡፡
መንፈሴን ለማረከው በሙዚቃ ስበት በፈቃድ መማረክ፤ የተወለድኩበት ዘመን፣ የተወለድኩበት አካባቢና በአካባቢውም ሰፍኖ የኖረው ከሙዚቃና ከሙዚቀኞች ጋር ቁርኝት የነበረው ሁኔታ አንዳች የሆነ አስተዋፅኦ አልነበረውም አልልም፡፡ መርካቶም ቢሆን፡፡ ስድስት ኪሎም ቢሆን፡፡ ጃንሜዳም ቢሆን፡፡ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ወይም መነ-አብቹ ወይም ራስ-ስዩም፣ አፈ-ንጉሥ ጥላሁን- ብዙነሽ በቀለ፣ ቀበናም፣ ዕንጦጦም፣ … ቢሆኑ፡፡ ዋሚ ቢራቱ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አበበ ቢቂላ፣ ሣህሌ ደጋጎ- አየለ ማሞ፣ ራስ ካሣ፣ ልዕለት ተናኘ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ… ሠፈርና መንደርስ ቢሆን፡፡
ደሞ አባቴ ሙዚቃ ወዳድ በተለይም ግሩም አድማጭ ነበር፡፡ እናቴም በትሆን ለራሷም ይሁን ለቤተሰባችን ደህና አንጎራጓሪ ነበረች፡፡ በተለይ ‹‹የአበሻ ጀብዱ›› የተሰኘውን መፅሐፍ ኢትዮጵያዊ ቅኔ መልሼ ያጣጣምኩበትንና ያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከእናቴ አንደበት የሰማሁትን ‹‹አብቹ ደራ ደራ…›› የተሰኘውን ሙዚቃና የዜማውን ኃያል የስበት ጉልበት መቸውንም የምረሳው አይደለሁም፡፡ በውስጤ መጠኑ የማይቀንስ፣ ዋጋው የማይዋዥቅ… የመንፈስ ምግብ ሆኖ የኖረ ነው፡፡ አልጠፋም፡፡ አልነጠፈም፡፡
የስበቱ ኃይል ሊገዳደሩት የማይቻል በመሆኑ ነው ከኑሮ ጋር፣ ከማንነት ጋር ተዛምዶ ኖሮት በጨቅላነቴ ዕድሜ በእኔነቴ ውስጥ መሽጎ መኖሩን ብቻ ሳይሆን የሚለመልምና የሚያንፀባርቅ ውበቱንና ቅርፁን በመኖር ዑደት ውስጥ መልሶ የሚያሳየኝ፡፡ ዋ ሙዚቃ! አልዘለቀበትም እንጂ አጎቴ ግርማ ጋሩማም እስከ ሕይወት ህቅታው ድረስ ግሩም ክራር መቺ የዐማርኛና የኦሮምኛ ሙዚቃዎች አቀንቃኝ ነበር፡፡ እነዚህ ክስተቶች፣ የሕይወትና ቅርብ የመኖር አጋጣሚዎችና ሙዚቃዊ ስበቶች ናቸው፤ በብዕር አሳንሰር አማከይነት ስለ ሙዚቃ ፍቅር የፈቃድ-ግዴታ ስበት ጉዳይ በጅምር ሃሌታ ደረጃ ጥቂት ሐሣብ እንዳነሳ የግድ ያሉኝ፡፡ እንዲያም ሆኖ ለነፍሴ በሙዚቃ ፍቅር ስበት ቁጥጥር ስር መውደቅ፤ ያለ አንዳች ጥርጥር የአባቴ ዜማን የማጣጣም ብቃት፣ የእናቴ ታላቅ ወንድም የሆነው የአጎቴ ጨዋታ ወዳድነትና ልዩ የአንጎራጎሪነት ወይም በዘፈኖች የመመሰጥ ዝንባሌ፣ የእናቴ የወጣትነቷ ጊዜ በረገዳዎች ችሎታ ጭምር የታገዘ የሙዚቃን ጥበብ ታላቅነት እስከ መመዘን ድረስ የሚተም ፈቃዳዊ ስሜት… አበርክቶው ታላቅ መሰለኝ፡፡
ያም ሆነ ያም ሆነ… በአበርክቶው መሠረት ደህና ጎረምሳ በነበርኩ ጊዜ ከአንድ ጎዳና ዳር ቆሜ በልዩ ስሜት ሳዳምጣቸው ከነበሩት ሙዚቃዎች መሀል ቀዳሚ ቦታ የሚኖራቸው፣ የሚልቁት፣ ረቂቆቹ… ትዝታና ወኔ ቃስቃሽ፣ ናፍቆትና መልካም ሐሣብ አመላለሽ፣ የፍቅርና የተብሰልስሎት ኑሮ ጓዞች አድራሽና መላሽ… ከሆኑት በላይም እየቀደሙ በሙዚቃ ፍቅር ስበት ኃያል ግፊት እየተመሩ ከፊት ከፊት ልሰለፍ ከሚሉት መሀል አንደኛው ውብሸት ፍስሐ የሚያንጎራጉረው ዘፈን ነበር፡፡ ያኔ የት ነበርኩ? ተነሰነይ ኮረብቶች ላይ፡፡ ጎንደር ሊማሊሞ በታች፡፡ ወገራና ስሜን አውራጃዎች ውስጥ በከፊል፡፡ ሊቦ ከምከም፡፡ በደንቢያ ወረዳ ሜዳዎች፡፡ ደብረ-ታቦር ጋሳይ፣ ወሮታ አዲስ ዘመን፣ ፈንዲቃ አየር- መወደቂያ፣ ከተከዜ ማዶ ከወልቃይት ጠገዴ- ‹‹ማረሻው ምንሽር መጎልጎያው ጓንዴ›› ባሻገር ሽሬ አውራጃ መነሻ ገጠር ቀበሌ ውስጥ… በሚገኙ ተራራዎችና ሸንተረሮች… ላይ፡፡ አይ የውብሸት ፍስሐ ዘፈን፡-
‹‹አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ?
ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ሳላይ፤
ከራስሽ አድርጊኝ ከድምድሙ ላይ
ከዐደሱ ከቅቤው እከብዳለሁ ወይ?
…. ….. ….. ….. …. ….. ….
ከአፋፉ ላይ ስዘልቅ ሁልጊዜ አይሻለሁ፣
አንድ ቀን መጥቼ እጠይቅሻለሁ›› እያለ የሚፈሰው፣ እያለ የሚንፎለፎለው… ዛሬም ድረስ ልክ ትላንት እንደሆነ ሁሉ ሆኖ የሚሰማኝ፤ ያው በሙዚቃ ፍቅር ልክፍት! በሙዚቃ ፍቅር ስበት እንጂ ዛዲያ በምንድን ምትኃታዊ ኃይል ነው? በምንም!
ደሞ እንደ ውብሸት ሁሉ በሙዚቃ ፍቅር ኃያል ስብት ጎትታ ነው ጎትጉታ… ዜኒት ሙሃባ የትላንቱን ሕይወት፡-
‹‹የኔ ድብቅ – የኔ ስውር
ገጸ ረቂቅ – ልበ ነብር
ተይዣለሁ በፍቅር ጣር
ና ና ና ና – ና ሽሽጌ፤ የኔ ሚስጥር…
የንጋት ኮከብ የብር ዕንክብል ዓይኖቹ
ልብ ይሰርቃሉ ጥርስ፣ ከናፍር ጉንጮቹ…›› ደግሞም፡-
‹‹ወፌ ላስቸግርሽ – አንዴ ተለመኚኝ
ለፍቅሬ መግለጫ – ዜማሽን አውሺኝ›› እያለች፤ ከነማኅበራዊ ኑሮ ስንክሳሩ የሙዚቃን ፍቅር ስበት ምስጢራዊ ዶሴ (መዝገብ) አምጥታ ከፊቴ ትቆልለዋለች፡፡ ላነበው እሞክራለሁ፡፡ ግን ልዘልቀው አይቻለኝም፡፡ እመሰጥበታለሁ፡፡ ሰምጬ የምቀርበት ሆኖ ይሰማኝኛ ከሆነ ሰመመን ውስጥ ስወጣ፤ ለራሴው ወይ ግሩም!… የግሩም ግሩም ነው እንጂ እላለሁ፡፡ በቃ የሙዚቃ ፍቅር ስበት ጉዳይ ኢምንት መልክና ገጽታው እንዲህና እንዲያም የሚመስል ነው፡፡ እነሆ ለኩርኮራ ያህል ክፍል አንድ (፩) ተይህ ላይ ቢቀነበብ ይበጃል፡፡ የስብቱ ነገር በእኔ በጭሮ አዳሩም ይሁን የሐሣቡ ተጋሪ ሊሆኑ በሚችሉ ተብሰልሳዮች ዘንድ ሊለጥቅ የሚችል እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ያሰንብትልኝ ፈጣሪ!… ክቡራንና ክቡራት አንባቢያንና የሙዚቃ አፍቃሪዎች፡፡