ያዕቆብ ብርሃኑ
የአንዳንድ ሰዎች ሕይወት የሆነ ገጽ የጎደለው ደራሲው የማይታወቅ የጠፋ መጽሐፍ የሚመስል ገጽታ አያጣም፡፡
‹ይመስላል ከተማው-
አሮጌ መጽሐፍ ግማሽ ገጽ የጠፋው› እንዲል ገጣሚው፡፡ ሕይወታቸው የቱንም ያህል ቢጻፍ የቱንም ያህል ቢለፈፍ ግን የተሟላ መልዕክት የለውም ፡፡ እነሱ የተጻፈላቸውን የተነገረላቸውን አይደሉም፡፡ ይሄን አይደለሁም እኔ እኮ እንዲህ ነኝ አይሉም-በጭጭታ ግዴለሽ መስለው ሲሲፐሳዊ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ሕይወታቸው የሆነ ግር የሚል ያልተዳሰሰ ስንኩል ገጽታ አያጣም፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ለእኔ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ነው፡፡ በእውን የስብሐት ለአብ ዕብደት የሚመስል ግርታ የታከለበት የዝግመት ኑረት ‹ልሕቀት ወይስ ውድቀት?› በእኔ እይታ ስብሐት የሚሳሳለትን መጫወቻ በጭካኔ ተነጥቆ ረዳት አጥቶ እንደሚያነፈርቅ ሕጻን ነበረ፡፡
የሚያሳዝነው ይህን ሽንፈቱን እንደምጥቀት በመቁጠር አጠገቡ ተቀምጠው ከአንደበቱ የሚወጡ ጣፋጭ ማባበያ ቃላትን እየቀለቡ ያስተጋቡልን ትንታጎች አንዳቸውም እንኳን የሽንፈቱን ምክንያት አለመረዳታቸው ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ ለስብሐት ለአብ የመጀመሪያ ምናልባትም የመጨረሻም ፍቅረኛው በነበረችው በንሸጣ ምንጩ ሀና ይልማ ምክንያት ነበር፡፡ ስብሐት በ1977 አካባቢ ለዶ/ር ታዬ አሰፋ እንዳጫወተው ከሀና ይልማ ጋር ከመለያየቱ፣ እድሜው 30 ዓመት እንኳ ከማለፉ በፊት ትኩሳትና ሌቱም አይነጋልኝን ጨምሮ አራት ወጥ ልብወለዶችና ዐሥራ አምስት የሚደርሱ አጫጭር ልብወለዶችን ጽፎ ነበር፡፡(ብሌን መጽሔት፣ ጥር 2007 ዓ.ም) ከሀና ይልማ ጋር ከተለያየ በኋላ በቀጠሉት ድፍን 40 ዘመናት ለእንጀራ ሲባል ጋዜጣ ላይ ከወረወራቸው ስብርባሪ ሀሳቦች ውጭ ምንም የታቀደ ቅርጽና ደርዝ ያለው መጽሐፍ አልጻፈም፡፡ በሀና ይልማ ሕልሙን የኪነት ንሸጣውን የተዘረፈው ሰው አጠገቡ ለነበሩት ግን የሆነ የተጃጃለ ካሪኬቸር(caricature) ገጸባህሪ ነበር፡፡
‹‹… በእኔ የደረሰብኝን ልጨምርልህ፡፡ እኔ ከገንዘብና ከሕግ በስተቀር የሚገዛኝ የለም፡፡ ከዚያ በላይ ፍቅር ነው የሚረታኝ፡፡ ሐና ግን ለእኔ ከዚያም በላይ ነበረች፡፡ እንዴት ልንገርህ እናቴ ማለት ነበረች፡፡ በሕይወትህ አንዳንድ ጊዜ ሙሉ ሰው የምትለው ሰው ይከሰታል፡፡ ለእኔ ሀና ይልማ ሙሉ ሰው ነበረች፡፡ በውበትም ዓይኔ ነበረች፡፡ በአካል ቁመናም ጭምር…›› (ማስታወሻ፣ ዘነበ ወላ ገጽ 138)
ስብሀት በዚሁ የዘነበ ወላ ማስታወሻ ላይ ሀና አጠገቡ ጋደም ብላ የጻፈውን ሲያነብላት ‹you are my author› ካለችኝ ለእኔ በምድር ከዚህ የሚበልጥ ሽልማት የለም› ይላል፡፡ ይህች የፍቅር አምላኩ፣ ዓለሙን ሙሉ ያደረገችለት ጣዖቱ ግን በአንድ የተረገመ አመሻሽ ዐሥር ሺህ ብሮችና የሞት መልዕክት የሚመስል የስንብት ደብዳቤ ብቻ ጥላለት በቅጡ እንኳን ሳትሰናበተው የሚወደውን የ3 ዓመት ልጁን ይዛ ከአገር ኮበለለች፡፡
በዚያች ምሽት የተሰበረው ልቡ በቀጠሉት አርባ ዘመናት እንኳን የተጠገነ አይመስልም፡፡ በቀጠሉት አርባ ዓመታት ምንም ግብ አልነበረውም፡፡ ለዕለት ውሎ ቁራሽ ዳቦና ጥቂት የጫት ዘለላ ካገኘ በቂው ነበር፡፡ በእርግጥ በየቅጽበታቱ በልቡ ላይ የደደረውን ቁዘማ ለማቅለል እንደ ጎልድመንድ ርካሽ ፍትወትን ያሳድድ ነበር፡፡ በገባኝ ልክ ይህ መንጠራወዝ ግን በሀና ምክንያት የገባበትን ወዲያው ወዲያው የሚያስደነግጥ የባዶነት አዝቅት የማምለጥ የማያቋርጥ የማያባራ የሽሽት ጉዞ እንጂ ሴሰኝነት አልነበረም፡፡ ስለ ደረሰበት የልብ ስብራት አምልጦት በሚመስል ሁነት ለዘነበ ወላ ከነገረው አንዲት ቃል ውጭ ለማንም ምንም ያለ አይመስልም፡፡
‹‹… ደብዳቤዎቹ አሁን የሉም፡፡ ከዓመታት በኋላ እኔ የጻፍኩላትን ደብዳቤዎች ሰብስባ ሰጠችኝና ተለያየን፡፡ በዚሁ ጊዜ አብዮቱ ፈንድቷል፡፡ ደብዳቤዎቹ ለእኔ ጥሩ ትዝታ ቢኖራቸውም እየቆዬ ውስጤ የሚተራመሰውን ስቃይ መቻል አቃተኝ፡፡ ስለዚህ ለዜና እናት እንኪ እሳት ለኩሺበት ብዬ ሰጠኋት፡፡…›› ገጽ 142
ስብሐት ለሀና ይልማ የነበረው ፍቅር ብዙዎቻችን በሩቁ እንደምንረዳው ፍትወት በሚያሰግረው የመውደድ ሲቃ የተቀነበበ አልነበረም፡፡ ሀና ይልማን እንደ ድንገት ያጣው ስብሀት ዘመኑን ሙሉ መጫወቻውን እንደተነጠቀ ህጻን ተጃጅሎ ወደ ውስጡ ሲያነፈርቅ ነበር፡፡ እኔ ግን አንዲህ አስባለሁ፡፡ ሀና ይልማ በዘመኗ ሁሉ ካሳካችውና ልታሳካ ከምትችለው ነገር ሁሉ በላይ በስብሐት ልብ ላይ የነበራት ልክ የለሽ አምልኮት አይበልጥም ይሆን? የዶ/ር ዮናስ አድማሱና የደራሲና ተርጓሚ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም የፍቅር ሕይወት ከስብሐት ጋር የሆነ የርቀት መመሳሰል እንዳለው ሳስብ ግር ይለኛል፡፡ ስብሃት መሻገር ችሎ በዚህች ሴት ምክንያት የደረሰበትን ባዶነትና ቁዘማ ቢከትበው ኖሮ እንዴት የሚያስጎመጅ መጽሐፍ በወጣው ነበር፡፡ ያስቆጫል!