በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ እንዲሁም የአፍሪካና አውሮፓውያንን ያሳተፈ በቆዳ ዘርፉና በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚገኙበት ኤግዚቢሽንና ባዛር የፊታችን ዓርብ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ለ14ኛ ጊዜ ባዘጋጀው አለም አቀፍ የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርኢት ከግንቦት 15-17 2017ዓ.ም ድረስ በሚሊኒየም አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ እንደሚካሄድ የማህበሩ ዋና ጸኃፊ አቶ ዳኛቸው አበበ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ራይዝ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ጌዴዎን በበኩላቸው እንዲህ አይነቱ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የንግድና ትርዒት በሀገራችን መካሄድ በዘርፉ ለተሰማሩ ነጋዴዎች አስመጪና ላኪዎች፣ አምራቾች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ገበያውን በአፍሪካና በአውሮፓ ጥሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸው ጎብኝዎችም በነጻ ለመገብየት የሚያስችል ሁኔታ ይኖረዋል ብለዋል።
ግንቦት 15/2017 ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው ንግድ ትርኢት እና ባዛር በመክፈቻው ዕለት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደሚገኙ የተናገሩት የአፍሪካ ራይዝ ኤቨንትስ የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ኣንተነህ ከተማ በሶስቱ ቀናት የፋሽን ትርዒት የሙዚቃና ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑ ገልጸው ህብረተሰቡ የነጻ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ በመምጣት መዝናናትና መገብየት እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የ”ኢትዮጵያ ታምርት!” መርህን የተከተለውና ወደተሻለ ደረጃ እየተጓዝን መሆናችንን እንደሚያሳይ የታመነበት የቆዳ ውጤቶች አውደ ርዕይ ዘርፉ ከእርድ ጀምሮ የተለያዩ መሰናክሎችና የጥራት ችግሮች ማነቆ እያሉበትንም ከበፊቱ መሻሻል በማሳየት ላይ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።
ሀገራችን በቆዳው ኢንዱስትሪ የደረሰችበትን ደረጃ ያሳያል የተባለው ይኸው ኤግዚቢሽንና ባዛር የፊታችን አርብ ለ14ኛ ጊዜ ከረፋዱ 4:00 ሰዓት በማርሽ ባንድ ደምቆ ይከፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።