ኑዛዜ የተነገረላቸው ሰዎች በሚያደርጉት የጋራ መግባባትና መስማማት የሟችን ኑዛዜ መቀየር/ማስቀየር ይችላሉ? ኑዛዜው የተደረገው በቃል ከሆነና ኑዛዜ የተላለፈላቸው ሰዎች ሳይስማሙ ቢቀሩ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በምን ማስረጃ ይመለከተዋል? (ተናዛዥ ሞተዋልና)… ኑዛዜውን አስነጋሪ ሊሞት በተቃረበ ወቅት የአእምሮ መታወክ ደርሶበት ከነበረ ኑዛዜው በሕግ ፊት ተቀባይነት ይኖረዋል? በኑዛዜ የሚተላለፍ የሀብት መጠን ገደብ አለው? ሌሎች የኑዛዜ ተካፋዮች ራቅ ባለ ስፍራ በሚኖሩበት ወቅት አንደኛው ወራሽ ልጅ ብቻውን በሟች አቅራቢያ ተገኝቶ ሊሞቱ የተቃረቡ አባቱን በማስፈራራት ለእሱ ያደላ ኑዛዜ እንዲያደርጉ (ከአንድ በላይ ምስክር ሳይኖር) ቢያስገድድ ተቀባይነት ይኖረዋል? በምን ማስረጃስ ይታያል?
መሠረት አዲሱ (አዲስ አበባ)
አንድ ሰው ከዚህ አለም በሞት ሲለይ በመሞቱ ምክንያት መብትና ግዴታዎቹ የማይቋረጡ ከሆነ እነዚህ መብትና ግዴታዎቹ ለወራሾቹ ይተላለፋሉ፡፡ ይኸውም የሟቹ መብትና ግዴታዎች ለወራሾች መተላለፍ የሚችልባቸው ሁኔታዎች የሚደነግገው የውርስ ህግ ዝርዝር በ1952 ዓ.ም በጸደቀው የፍትሃ ብሔር ሕጋችን ወስጥ አንድ ክፍል ሆኖ ተቀምጦ እናገኘዋለን፡:
በፍትሃ ብሄር ህጋችን መሰረት ውርስ በሁለት አይነት መንገድ የሚተላለፍ ሲሆን እነሱም በኑዛዜ እና ያለ ኑዛዜ ናቸው፡፡ በፍትሃ ብሄር ህጉ ከ842-856 ድረስ ባሉት አንቀጾች ውስጥ ሟች ኑዛዜ ሳይተው ቢሞት ንብረቱን ማን መውረስ እንዳለበት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
እንዲሁም የሟች ንብረት ለወራሾች የሚተላለፍበት ሌላው መንገድ ኑዛዜ በመናዘዝ ሲሆን ዝርዝር ሁኔታዎቹም ከአንቀጽ 857-941 ድረስ ባሉት አንቀጾች ስር ተቀምጠዋል፡፡
በዛሬውም እትማችን ከአንባቢያችን የደረሰንን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የኑዛዜ ህግን እንዳስሳለን፡፡
የኑዛዜ ውርስ፡- በፍትሃ ብሄር ህጉ ከ857-941 ድረስ ባሉት አንቀጾች ስር የተደነገገ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ላይም ኑዛዜ በህግ ፊት የጸና እንዲሆን መሟላት ያለባቸው ነገሮች ተቀምጠዋል፡፡
እነሱም፡-
ኑዛዜ በሟች በራሱ የሚደረግ ህጋዊ ድርጊት ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው ለሌላ ሰው በስሙ ኑዛዜ ማድረግ፣ መለወጥ ወይም መሻር አይችልም፡፡ ሟች ይህን ግላዊ ባህርይ ያለውን ድርጊት /ኑዛዜን/ ለሌላ ሶስተኛ ሰው እንዲያደርግለት ስልጣን ሊሰጠው አይችልም፡፡ በሟችና በሌላ ሰው መካከል ይህን አስመልክቶ የተደረገ ስምምነት ቢኖር በህግ ፊት ዋጋ አይኖረውም ማለት ነው ፡፡
እንዲሁም ኑዛዜ የተደረገላቸው ሰዎች በሚያደርጉት የጋራ መግባባትና ስምምነት የሟችን ኑዛዜ መቀየር አይችሉም፡፡
ሶስተኛው ሰው የሟች ሞግዚት ቢሆን እንኳን በዚህ ሞግዚት በሆነለት ሰው ስም ኑዛዜ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ሰዎች አንድ ብቻ በሆነ ፅሁፍ የተናዘዙ እንደሆነ ኑዛዜው ዋጋ የለውም (ፈራሽ ይሆናል ማለት ነው)፡፡
1. ኑዛዜ ለማድረግ ችሎት ማስፈለጉ፡፡
በህጉ መሠረት አንድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ 15 አመት ካልሞላው በስተቀር ኑዛዜ ሊያደርግ አይችልም፡፡ 15 አመት ያልሞላው ልጅ ኑዛዜ ፈጽሞ በሚገኝበትም ወቅትም ያደረገው ኑዛዜ በህግ ተቀባይነት የሌለው ፈራሽ ይሆናል ማለት ነው ፡፡
እንዲሁም ሞግዚቱ 15 ዓመት ያልሞላውን ልጅ ኑዛዜ እንዲያደርግ ፈቃድ ሊሰጠው አይችልም፡፡ አንድ ሞግዚት አካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ የዕለት ጉዳዩን በተመለከተ ብቻ ነው ልጁ ውሎችን እንዲፈፅም መፍቀድ የሚችለው፡፡ ስለሆነም ኑዛዜ ደግሞ ከነዚህ የዕለት ጉዳዮች ውስጥ ስለማይጠቃለል ሞግዚቱ አካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ ኑዛዜ እንዲፈፅም የመፍቀድ ስልጣን በህግ የለውም ማለት ነው፡፡
• በፍርድ የተከለከለ ሰውም ልክ አካለ መጠን እንዳልደረሰ ሰው ኑዛዜ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ኑዛዜው የተደረገው ግን በፍርድ ክልከላ ከመደረጉ በፊት ከሆነ ኑዛዜው ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
• ፍ/ቤት በፍርድ የተከለከለ ሰው ከመከልከሉ በፊት ያደረገው ኑዛዜ ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች የተነሳ ካላፈረሰው ኑዛዜውን በከፊል ወይንም በሙሉ ሊያፀናው ይችላል፡፡ ሆኖም ፍ/ቤቱ ዋጋው ከአምስት ሺህ የኢትዮጵያ ብር በላይ የሆነውን የኑዛዜ ስጦታ ሊያፀናው አይችልም፡፡
• ነገር ግን አንድ በህግ የተከለከለ ሰው ማለትም በወንጀል ተቀጥቶ ንብረቱን እንዳያስተዳድር ህግ የከለከለው ሰው ኑዛዜ የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡
2. ይህ ሰው በምንም አይነት ወንጀል ቢከሰስ እንዲሁም ምንም አይነት ቅጣት ቢወሰንበት ቅጣቱ ኑዛዜ እንዳያደርግ የሚከለክል እስካልሆነ ድረስ ኑዛዜ የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡
ኑዛዜ ሊፈጸም የሚችል መሆን ያለበት ስለመሆኑ
3. ሌላው ኑዛዜን ፈራሽ ሊያደርጉ ከሚችሉባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ኑዛዜው ለመፈጸም የማይችል መሆን ነው፡፡ አንድ ሰው የሚያደርገው ኑዛዜ መፈፀም የሚችል ኑዛዜ ካልሆነ ኑዛዜ ማድረጉ ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህም ነው ህጉ ኑዛዜ በሚገባ ተጠቃሚውን ወይም ጉዳዩን ካላመለከተ እንዲሁም አፈፃፀሙ የማይቻል ከሆነ ፈራሽ ይሆናል በማለት የደነገገው፡፡ ለምሳሌ ሟች ቤቴ ለእህቶቼ ይሁን ብሎ ቢናዘዝ ብዙ ቤቶችና 4 እህቶች ቢኖሩት የትኛው ቤት ለየትኛዋ እህት እንደሚሰጥ ግልፅ ስላልሆነ ኑዛዜውን ለማስፈፀም አይቻልም፡፡ በሆነ መንገድ ሟች የትኛውን ቤት ለየትኛዋ እህቱ ማለት እንደፈለገ ለማረጋገጥ ከተቻለ ግን ፍ/ቤት ኑዛዜውን ሊያፀናው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ተናዛዥ አንድ መኪናውን ለአንድ ሰው ከተናዘዘ በኋላ በዛው ኑዛዜ ውስጥ ይህንኑ ንብረት ለሌሎች ሰዎች ቢናዘዝ ይህ ኑዛዜ አፈፃፀሙ የማይቻል ስለሆነ ፈራሽ ይሆናል ማለት ነው፡፡
4. ኑዛዜ ለህግ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ መሆን የለበትም፡፡
የአንድ ሰው ኑዛዜ በህግ ያልተፈቀደ ወይንም ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ መሆን የለበትም፡፡ ኑዛዜ ህገ ወጥና ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ ሆኖ ከተገኘ ፈራሽ ይሆናል፡፡
ለምሳሌ፡- አንድ ሰው በኑዛዜ ማስተላለፍ የሚችለው የራሱን ንብረት ሲሆን የራሱ ያልሆነን ንብረት የሚያስተላልፍ ኑዛዜ መናዘዝ ይህ በህግ ስለማይፈቀድ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል፡፡
5. በማስገደድ የተገኘ ኑዛዜ፡-
ኑዛዜ በተናዛዥ ንጹህ ፍላጎት የተመሰረተና ከማናቸውም ተፅዕኖ ነጻ ሆኖ የሚፈፀም ህጋዊ ድርጊት ስለሆነ ከነፃ ፍላጎት ውጪ የተሰጠ የኑዛዜ ቃል በህግ ውጤት የሌለውና ፈራሽ ነው፡፡ በመሆኑም ኑዛዜ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል አንደኛው ተናዛዡን በማስፈራራት ለሱ ያደላ ኑዛዜ እንዲናዘዝ ቢያደርግ ግለሰቡ ሟቹን ያስፈራራ መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ኑዛዜው በተናዛዥ ንጹህ ፍላጎት የተገኘ ሳይሆን በማስፈራራት የተገኘ በመሆኑ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ይህን በተመለከተ የተነሳውን የአንባቢያችንን ጥያቄ ስንመለከት ሌሎች የኑዛዜ ተካፋዮች በአቅራቢያው ባለመኖራቸው አንደኛው ወራሽ ልጅ በአቅራቢያው ተገኝቶ ለሱ ያደላ ኑዛዜ እንዲናዘዙ አባቱን ያስፈራራ እንደሆነ ሌሎቹ የኑዛዜ ተካፋዮች ኑዛዜው በተናዛዥ ንጹህ ፍላጎት ያልተመሰረተና በማስገደድ (በተጽዕኖ) የተሰጠ ኑዛዜ መሆኑን በማስረዳት ኑዛዜው ፈራሽ እንዲሆን ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም የቀረበለትን አቤቱታ መሰረት በማድረግ ኑዛዜው በማስፈራራት የተገኘ መሆኑን ከተረዳ ኑዛዜውን ሊሽረው ይችላል ማለት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሟች ያኖሩት ግልጽ ኑዛዜ የሆነ እንደሆነ ህጉ ኑዛዜው ከአራት ምስክሮች ፊት እንዲፈጸም እና ምስክሮቹም ፊርማቸውን ወዲያው እንዲያኖሩ የሚያዝ በመሆኑ የዚህ ድርጊት አለመፈጸም ኑዛዜውን ፈራሽ ስለሚያደርገው ሌሎቹ የኑዛዜው ተካፋዮች ይህ አለመፈጸሙን መሰረት በማድረግ ኑዛዜው እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡
6. በስህተት የተሰጠ ኑዛዜ፡-
በስህተት የተሰጠ ኑዛዜ ቃል ኑዛዜን ለማፍረስ ከሚያበቁት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህንንም ስንል አንድ ስህተት ኑዛዜን ለማፍረስ የሚያበቃው ወሳኝና መሠረታዊ ሲሆን ነው እንጂ ማናቸውም አይነት ስህተቶች ኑዛዜን ያፈርሳሉ ማለት አይደለም፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ኑዛዜን ፈራሽ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች በተጨማሪ ፍርድ ቤት ገምግሞ ኑዛዜን በከፊልም ሆነ ባጠቃላይ የሚሸርባቸው ሁኔታዎች አሉ፡:
እነዚህም ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
ሟች ለሞግዚቱ ወይንም ለአሳዳሪው ጥቅም ያደረገው ኑዛዜና ተናዛዥ የሞተው 2ዐ ዓመት ሳይሞላው ከሆነ፡፡
ሟች ከመሞቱ አስቀድሞ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የህክምና ወይም የመንፈስ እርዳታ ላደረጉለት ሰዎች ያደረገው የኑዛዜ ቃል፡፡
በሕግ ውል ለማዋዋል ስልጣን ለሰጠው ሹም የተደረገ ኑዛዜ፡፡
ለኑዛዜ ምስክሮች የተደረገ ኑዛዜ፡፡
ሟች ከበፊት ጋብቻ የተገኙ ተወላጆች እያሉት ለኋላ ባል ወይንም ሚስት ጥቅም ያደረገው/ያደረገችው የኑዛዜ ቃል፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት ፍ/ቤት ሁኔታዎችን የመመርመርና ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው የኑዛዜ ቃሉን የመቀነስ ወይንም የመሻር ስልጣን አለው፡፡
ከነዚህ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ውጪ አንድ ሰው ኑዛዜውን ባደረገበት ወቅት የመንፈስ መጫን ተደርጎበታል ተብሎ ኑዛዜ እንዳይፈርስ ሕጉ በግልፅ ይከለክላል፡፡
እንዲሁም ተናዛዡ ኑዛዜውን ባደረገበት ወቅት የታወቀ እብድ ካልነበረ በስተቀር የአእምሮ ጉድለት ነበረበት በሚል ምክንያት ኑዛዜ ሊሻር እደማይችል አንቀጽ 863 ላይ ተደንግጓል፡፡
አንድን ኑዛዜ በህግ ፊት ተቀባይነት እንዲኖረው ከላይ በዝርዝር ያየናቸው ነጥቦች መሟላት ያለባቸው ሲሆን ከነዚህ ሁኔታዎች አንዱ ሳይሟላ ቢቀር አንድን ኑዛዜ ህጋዊነት ያሳጣዋል ማለት ነው፡፡
3.2.5. የኑዛዜ ዓይነቶች /ፎርሞች/
በሕጉ መሠረት የኑዛዜ አይነቶች ሶስት ሲሆኑ እነሱም፡-
በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ
በተናዛዡ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ
በቃል የሚደረግ ኑዛዜ ናቸው፡፡
ሀ) በግልፅ የሚደረግ ኑዛዜ
አንድ ኑዛዜ በህግ በግልፅ ኑዛዜነቱ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ኑዛዜው በተናዛዡ ወይንም ተናዛዥ እየተናገረ በሌላ በማናቸውም ሰው የሚፃፍ ነው፡፡
ኑዛዜው በተናዛዥና በአራት ምስክሮች ፊት ተነቦ ይኸው ስርዓት መፈፀሙን የሚያመለክት መሆን አለበት፡፡
ተናዛዥና ምስክሮቹ በኑዛዜው ላይ ወዲያውኑ ፊርማቸውን ማኖር አለባቸው፡፡
ኑዛዜው የተፈጸመበት ቀን ወርና ዓመተ ምህረት በኑዛዜው ላይ መገለጽ ይኖርበታል፡:
ከነዚህ መስፈርቶች መካከል አንዱ ሳይሟላ ቢቀር በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ ማሟላት የሚገባውን መስፈርት ያላሟላ በመሆኑ በህግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
ለ) በተናዛዥ ፅሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ፡-
በተናዛዥ ጽሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ በህግ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
በተናዛዥ ጽሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ ሊደረግ የሚችለው በራሱ በተናዛዥ ፅሁፍ ብቻ ነው፡፡
በጽሁፉም ላይ ኑዛዜ መሆኑ በግልፅ መገለፅ አለበት፤ ይኸውም ኑዛዜውን ከተናዛዥ ሌሎች ሰነዶች ለይቶ ለማወቅ እንዲያስችል ነው፡፡ የኑዛዜው ሰነድ ኑዛዜ እንደሆነ በግልፅ ካልተመለከተ በህግ ፈራሽ ይሆናል፡፡
በእያንዳንዱ ገፅ ላይ ተናዛዥ ቀን መፃፍና መፈረም ይኖርበታል፡፡ ህጉ ይህንን ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠበት ምክንያት የቀረበው ሰነድ የሟች መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ እንዲቻል ለማድረግ ነው፡፡
ተናዛዥ በታይኘ (በኮምፒውተር) ከሆነ ኑዛዜውን የፃፈው የኑዛዜ ሰነድ በእያንዳዱ ገፅ ላይ በራሱ የእጅ ፅሁፍ ኑዛዜውን ያዘጋጀው ራሱ መሆኑን ማመልከት አለበት፡፡
እንዲሁም ኑዛዜው መቼ እንደተጸፈ የሚያስረዱ ቀን ወርና አመተ ምህረት በኑዛዜው ላይ መጻፍ ይኖርበታል እነዚህና እነዚህን መሰል መገለጫዎች ከሌሉ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል፡፡
በተናዛዥ ጽሁፍ የተደረገ ኑዛዜ ተናዛዡ ኑዛዜውን ካደረገ በኋላ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ወይም ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው ክፍል ተመዝግቦ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ይህ ካልተፈጸመ ኑዛዜው ውድቅ ነው የሚሆነው፡፡
ሐ) የቃል ኑዛዜ፡-
የቃል ኑዛዜ ማለት አንድ ሰው የሞቱ መቃረብ ተሰምቶት የመጨረሻ ፈቃድ ቃሎቹን ለሁለት ምስክሮች የሚገልጽበት ነው፡፡ አንድ ሰው የቃል ኑዛዜ ሊያደርግ የሚችለው የተወሰኑ ነገሮችን በተመለከተ ብቻ ሲሆን እነሱም፡-
የቀብሩን ስነ ስርዓት አስመልክቶ ትዕዛዝ መስጠት
ከአምስት መቶ ብር የማይበልጡ የተለያዩ የኑዛዜ ስጦታዎችን መስጠት እና
አካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች አስተዳዳሪን ወይንም ሞግዚት የሚሆኑ ሰዎችን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ውጪ የቃል ኑዛዜ ቢደረግ ፈራሽ ነው፡፡ ይኸም ማለት የኑዛዜው ቃል እንዳለ ይፈርሳል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በቃል ኑዛዜ ከ500 ብር በላይ የኑዛዜ ስጦታ ቢያደርግ ይህ ስጦታ እስከ አምስት መቶ ብር ድረስ ያለው ይፀናና ከዚያ በላይ ያለው ስጦታ ግን እንዳልተደረገ ይቆጠራል፡፡
ኑዛዜው የተደረገው በቃል ከሆነና ኑዛዜ የተላለፈላቸው ሰዎች ሳይስማሙ ቢቀሩ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በምን ማስረጃ ይመለከተዋል? (ተናዛዥ ሞተዋልና) ለሚለው የአንባቢያችን ጥያቄ በቃል የተደረገው ኑዛዜ ከላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች ውጭ ከሆነ ፈራሽ ሚሆን ሲሆን ኑዛዜ በተደረገላቸው ሰዎች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ፍርድ ቤቱ በወቅቱ ኑዛዜው ሲፈጸም የነበሩትን ምስክሮች ቃል በመቀበል ጉዳዩን ለመመርመር ይችላል፡፡
እንዲሁም በቃል ከተደረገ ኑዛዜ በስተቀር በሌሎቹ የኑዛዜ አይነቶች ተናዛዡ ያለምንም ገደብ ንብረቱን ማውረስ ይችላል ማለት ነው፡፡
የኑዛዜዎች መሻር እና ውድቅ መሆን፡-
የፍትሃ ብሄር ህጉ ኑዛዜዎች ሊሻሩ እና ውድቅ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር አስቀምጧል እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ተናዛዡ ኑዛዜ ባደረገበት ፎርም አይነት ኑዛዜውን የሻረ እንደሆን ኑዛዜው እንደተሻረ ይቆጠራል፡፡
ተናዛዡ የኑዛዜውን ወረቀት በመቅደድ፣ በመሰረዝ ወይም በማጥፋት ሊሽር ይችላል፡፡
ተናዛዡ በኑዛዜው የተገለፀውን ንብረት ከመሞቱ በፊት ለሌላ ሰው ቢያስተላልፈው ወይም ቢሸጠው ኑዛዜው እንደተሻረ ይቆጠራል፡፡
በቃል የተደረገ ኑዛዜ ከተደረገበት ከሶስት ወር በኋላ ተናዛዡ በዚህ ጊዜ በህይወት ያለ ከሆነ ኑዛዜው ውድቅ ነው የሚሆነው፡፡
በተናዛዥ ጽሁፍ የተደረገ ኑዛዜ ተናዛዡ ኑዛዜውን ካደረገ በኋላ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ወይም ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው ክፍል ካልተቀመጠ ውድቅ ነው፡፡
ኑዛዜ ከተደረገ በኋላ፤ ተናዛዥ ልጅ ቢወልድና ወይም የልጅ ልጅ ተወልዶ በምትክነት ለመውረስ ቀርቦ ይህ ልጅ /በወኪሉም ቢሆን/ ውርሱን ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆነ ኑዛዜው ቀሪ ይሆናል፡፡
ሟች ለባል ወይም ለሚስት ያደረጉት ኑዛዜ ጋብቻው በሞት ሳይሆን በሌላ ምክንያት ቢፈርስ ኑዛዜው ቀሪ ይሆናል፡፡
ኑዛዜ የተደረገለት ሰው ከተናዛዡ በፊት ከሞተ ኑዛዜው ቀሪ ይሆናል ማለት ነው፡፡