አፍሪካ ወጣትና በፍጥነት እያደገ የሚሄድ ሕዝብ፣ የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሃብት፣ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን እያስመዘገበ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል ያላት አህጉር እንደመሆኗ አካታች የሆነ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን፣ ዘላቂ ዕድገትን እና የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት ከፍተኛ አቅም አላት ።
ይህን ዕድል ለመጠቀም የክህሎት ልማት ያለውን ወሳኝ ድርሻ በመገንዘብ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን (AUC) እና ቁልፍ ባለድርሻ አካላት የአፍሪካን የክህሎት ለውጥ አጀንዳ ለማራመድ የአፍሪካ ክህሎት ሳምንት (ASW) በ2024 ዓ.ም ልዩ፣ አህጉር አቀፍ መድረክ ሆኖ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡
በኖቬምበር 2024፣ የአፍሪካ ህብረት የትምህርት እና ስልጠና ሚኒስትሮች ባደረጉት ምክክር ‹‹የአፍሪካ ክህሎት ሳምንት›› በሀገር፣ በክልል እና በአህጉራዊ ደረጃ በየዓመቱ የሚታወቅ ሁነት እንዲሆን በይፋ አጽድቀዋል ።
ሁነቱ በክህሎት ልማት እና በሥራ ስምሪት ላይ ሰፋፊ ውይይቶች ይካሄዱበታል፤ ይህም አካታች የኢንዱስትሪ እድገትን ከማረጋገጥ ፣ፈጠራን በአህጉሪቱ ከማስፋፋትና ብቁ የሰው ኃይልን ከማፍራት አንፃር ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ክህሎት ሳምንት በመላው አህጉሪቱ የክህሎት ልማትን እና ሥራ ፈጠራን ለማሳደግ በሚያስችሉ የተለያዩ አጀንደዎች ላይ በማተኮር በጋና ፣ አክራ ተካሂዷል፡፡
ከመላ አፍሪካ የተውጣጡ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ ምሁራን፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች፣የወጣቶች ተወካዮችና ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በሁነቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
‹‹ሁለተኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት 2025›› ከጥቅምት 3 እስከ 7/2018 በአዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት ”የአፍሪካን የኢንዱስትሪ አቅም ማጎልበት፣ ለፈጠራ፣ ለእድገት እና ለዘላቂነት ክህሎት ልማት’’ በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚንስቴር ከአፍሪካ ህብረት ጋር በጋራ ያዘጋጁት ይህ,ታላቅ አህጉራዊ ሁነት የክህሎት እና የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊዎች፣ የክህሎት ልማት ጥራት እና አካታችነት፣የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ሀብት መጋራት፣ ተቋማዊ ልማት፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ይካሄዳል፡፡