የኢት ሬዲዮ ዜና ፋይል አጋሮቹ ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ ጎበኘነው

Date:

የዜና ፋይሎቹና የሚዲያ ቤተሰቦች አጋርነት የተገለጠበት! ወዳጅና የስራ ጓዳችን ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ ከቤተሰቡ ተቀላቅሏል፤ የኢት ሬዲዮ ዜና ፋይል አጋሮቹም ጎበኘነው።

ሰመድን እንኳን ለቤትህ አበቃህ ልንለው ሄደን ከትናንት እስከ ዛሬ ሞያን ከሀገር ማገልገል ጋ አንስተን በቁጭት አውግተናል።

በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይል የስራ ውጥረት ቢኖርብንም በእኛ መካከል ወንድማማቻዊ የእህትማማችነት ማህበራዊ ቅርርቡ መጽሐፍ መዋዋስ፥ መመካከርና ቀልድ ጨዋታችን ያሉብን ጫናዎቻችንን ያስረሱናል መሰለኝ።።

የአመት እረፍታችን በተደጋጋሚ ሾቆብናል፥ አንዳንዴ ውጥረቱ በዝቶ መታመምም መሞትም አይቻልም፥ አመት እረፍትም አይፈቀድም የምንባልበትም ወቅት ነበር፤ ጣቢያውን ለቀን ከስራ ስንወጣ ቅዳሜና እሁድን አርፈን ስለማናውቅ ተዝናንቶ እንዴት ማሳለፍ እንደሚቻልም የቸገረን ነበርን።

በዓላትማ ከቤተሰብ ጋ ማሳለፍ ብርቃችን ነበር፤ በዚህ ጉዳይ አብዱልሰመድና ተፈሪ ለገሠ የባልደረቦቻቸውን ቅዳሜ እና እሁድ ብሎም በበአላት ቀን ተክተው በመግባት ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው።

መደበኛ ስለሀገር እና ሕዝብ በያገባናል መቆርቆር በሚመነጩ ዘገቦቻችን ሳቢያ ከላይ መንግስታዊ አስተዳደሩ ተጠያቂ ሊያደርጉኝ እግር በእግር ይከታተሉኛል ይላል።

በሌላ በኩል ሕብረተሰብ ደግሞ አቤቱታዎች ዝርዝር ጥልቀት አግኝተው ተጎልጉለው አልወጡም ብሎ ይወቅሳል። እናም እንደ ቡሄ ዳቦ በመሀል መብሰል ነው እንላለን።

ያኔ በጋራ ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች አንስቶ እርስ በርስ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለን ክፍተቶቻችንን ተሸፋፍነን፥ ጎዶሏችን ተሞላልተን፥ ስንቸገርም ተደጋግፈን እንደ እንድ ትልቅ ቤተሰብ አብረን በፍቅርና መደጋገፍ ያሳለፍነውን ጊዜ በምልሰት ገርበን አውግተናል።

ጭንቅ ውስጥ ከቆየች ባለቤቱ ነፂ እና ከሚያሳሱ ልጆቹ ዘንድ በኪዳነ ምህረት አመታዊ ንግስ – ምሽቱ ገፍቶ አብዱልሰመድ መሀመድን እግዚያብሔር ይመስገን እኛም በሰላምና ስስት አግኝተነዋል።

ወዳጃችን ሰመድ ደብዛው ጠፍቶ የት ይሆን? በሚል መላ ጠፍቶን በነበረበት አስጊ ሰአት አብራችሁ ከሳምንት በላይ በነበረ ውጣ ውረድ ተጨንቃችሁ የነበራችሁ ሁሉ፤ ስለሆነው የጭንቅ ማግስት ፋታ እግዚያብሔር ዋጋ ያድርግላችሁ!

በሀገሬ ኢትዮጵያ መቼም ተስፋ አልቆርጥም፤ እንጀራዬ ብዬ በኖርኩለት ጋዜጠኝነትም እንዲሁ።

ማርቲን ሉተርኪንግ “ሕልም አለኝ”- እንዳለው እንደ ሞያተኞች እንኳንም የሕዝብ አገልግሎት ከልቤ የምሰጥበት – የሚዲያ ሞያ ላይ – እንኳን ሆንኩ ብለው የሚያመሰግኑበት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ሚዲያ በነጻ ዘገባ የሚያቀርብበት ቀን ይመጣል።

እርግጥ ነው – ነፃነት ወዳጆችና የእውነት ጠበቆች በኢትዮጵያ ሞልተው ስለሀገር ልዕልና ሲሉ እንደልብ እንዲጻፍ፥ በነጻነት ዜጎች ሀሳባቸውን እንዲገልጹ፥ ሕዝብም መረጃ ላይ ተመስርቶ ፥እንዲወስን ለሀሳብ ብዝኀነት የሚቆሙ ሞያተኞች የሚበዙበት ቀን ይመጣል።

ወይ በፍርሃትና አሊያም በቲፎዞ (Sway between Fear & Favor) መሃል ዥዋዥዌ የሚጫወቱ መገናኛ ብዙኀናት ለሀገርም ሆነ ለመንግስትና ሕዝብ ፋይዳ እንደማይኖራቸው ሁሉም ባለድርሻ አካል – እመኛለሁ አንድ ቀን የጋራ መገንዘብ ላይ ይደርስና ቁርጠኛ አቋም ይያዛል።

አምናለሁ አንድ ቀን – ሚዲያ እንደ ደሴት ከሚታይበት ሁኔታ ወጥተን – ሀሳብን በነጻ የመግለፅ መብት፥ መረጃ የማግኘት መብት፥ ነጻ ዳኝነት፥ ፍትሐዊ አስተዳደር፥ በነፃ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት በሌለበት የሚዲያ ነጻነትን ማሰብ ተምኔታዊነት (Utopia) ስለመሆኑ አንድ ቀን እንደሀገር የጋራ ግንዛቤ እንይዛለን።

ስለዚህ የሚዲያ ነፃነት ፋይዳን ለመረዳት ከመስኮት ማዶ ከአድማስ ባሻገር አናማትርም፤ መፍትሔው ቁጭ ብሎ በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ነው፤ ችግሩ እኛው ጋ እንዳለ ሁሉ – መላውንም ሰውሮብን እንጂ ምንም የሮኬት ሳይንስ አይደለም፤ ለጥያቄዎቻችን መልሱም ከእጃችን እኛው ጋ ነው።

ማርቲን ሉተር ኪንግ ያልተመነዘረ ቼክን – በተግባር መሬት ላይ ካልተተረጎመ የሕገ መንግስት ቃል ኪዳን ጋር አናፅሮ ተናግሮ ነበር። ይህ ‘The Uncashed Cheque like Unfulfilled Promise of the Constitution’ መሆኑ ነው።

ተስፋ አደርጋለሁ አንድ ቀን! አምናለሁም – የሕገ መንግስቱ ይዘት በሚለው ልክ – በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ለመብቶቻችን መከበር ቀናኢ የሆነ አስተዳደር እውን ሆኖ – ከእንግዲህ ዜጋና ሕዝብ የማይከብርበት ሀገር ሀገር ሆኖ አይቀጥልም የሚለው ላይ የጋራ መረዳት እንፈጥር ይሆናል፤ ግጭትም ከወቅታዊ አጀንዳችን ወጥቶ ወደ ታሪክ መጽሓፋችን ገብቶ ይቀርም ይሆናል።

በሂደት መንግስታዊ አስተዳደራችን ተገማች (Predictable) ፥ ግልፅ የአስተዳደር ሥርአትን የዘረጋ (Transparent) እና ተጠያቂነትን (Accountable) ለራሱ መንግስታዊ ቆንጆ መልኩ ሲል እንደሚያሰፍን ይገመታል።

ጽኑ ባለአቋም ሞያተኛው ጌታሁን ንጋቱ፥ የጂኦ ፖለቲክስ መረዳቱና በወግ አዋቂነት የተለየው የኔነህ ከበደ፥ ታታሪና ልበ ቀናው ቢንያም ከበደ፥ ቆፍጣኒት ቁም ነገራሟ ነፃነት ፈለቀ እና የስራ ቡልዶዘሩና የዋሁ አብዱልሰመድ ጋር ሆነን አይረሴ ጊዜ ከቤተሰቡብ አባላት ጋር አብረን አሳልፈናል።

ለ11 ቀናት ሰመድ ከቤቱ ተለይቶ በእስር በቆየባቸው ቀናት ቤተሰቡን ከልብ በሆነ አይዟችሁ ባይነት ስትደግፉ ለነበራችሁ የዜና ፋይልና የሚዲያ ቤተሰቦች ሁሉ የአምላክ ተራዳኢነት ለችግራችሁ ቀድሞ ይድረስላችሁ!

ቁምላቸው ከበደ፥ ነጋሳ ግሥላ፥ ቢንያም ከበደ፥ እሸቱ ገለቱ፥ የእኔነህ ከበደ፥ ምናሴ (ቹቹ)፥ ጌታሁን ንጋቱ፥ ነጻነት ፈለቀ፥ ዋሲሁን አራጌ፥ ኃ/አምላክ ካሳዬ እና ጋሻው ተፈራ በሀሳብም ሆነ በተቻለ አቅምም የሰመድ ቤተሰብን አይዟችሁ ለማለት ላሳያችሁት ቀና ድጋፍ አክብሮታችን ይድረሳችሁ።

እንደ ሰመድ ሁሉ የሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጁ ዮናስ አማረም እንዲሁ ታፍኖ ተወስዶ ለ10 ቀናት ደብዛው ጠፍቶ ቆይቶ በተመሳሳይ ቀን ነሐሴ16 ማታ 3:00 ሰአት ላይ መለቀቁ ታውቋል።

እሸቱ ገለቱ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በፖለቲካዊ ሳይሆን በቴክኒካዊ መንገድ መፈታት አለበት

በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ፣ እና የመካከለኛው ምስራቅ...

የ7 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አለመከናወኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሚተዳደሩ 7 የጋራ መኖሪያ...

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በ80 ዓመታቸው ከዚህ...