በአንድ ወቅት አንዲት የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኛ ወደ ከፍታ ወጣቶች የጤና አገልግሎት (YFHS) መጣች። በቆይታዋም መሠረታዊ የሚባሉ ምክሮችና ጠቃሚ መረጃዎችን መካፈል ቻለች፡፡ ደፋሯ እንስት ከአገልግሎቱ የቀሰመችውን ትምህርት ለማስፋት ያግዛት ዘንድም በሌላ ጊዜ ያጋጠማትን ከወር አበባ መዛባት፣ ከከባድ ደም መፍሰስ እና ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር ጾታዊ ተራክቦ ከመፈጸም ጋር በተያያዘ የደረሰባትን ችግር መፍትሔ ለማግኘት ተከሰተች፡፡
ግለሰቧ ያጋጠማትን ጉዳይ የተገነዘበው የከፍታ ወጣቶች የጤና አገልግሎትም፣ ወዲያውኑ ተገቢውን ምክር እና ድጋፍ ወደ ማድረግ ገባ፡፡ በሒደቱም ስለ ቤተሰብ ምጣኔ እና በጾታዊ ተራክቦ አማካኝነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖችን ስለመቆጣጠር ብሎም ስለሌሎችም ወሳኝ ጉዳዮች የምክር አገልግሎት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ እንድታገኝ ተደረገ፡፡ በእነኚህ የግል ምክርና የትምህርት ጊዜያት፣ በተለይም የወር አበባ መዛባትን ሊያስከትሉ ስለሚችሉት እንደ ጭንቀት፣ የሆርሞን መዛባት ወይም ሌሎች የጤና ሁኔታዎችን ስለተመለከቱ ምክንያቶች ተገቢውን ግንዛቤ እንድትይዝም ተደረገ፡፡
ከዚህ ሒደት በኋላም፣ የባለሙያ ሕክምና አስፈላጊነትን በመረዳት የከፍታ ፕሮጀክት አጋር በኾነ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ አምርታ በጤና ባለሙያ መታየቷ አስፈላጊነቱ ታመነበት። ወደ ጤና ጣቢያው አምርታ ጤናዋን የተመለከተ ሙሉ ምርመራ ከማድረግ ጀምሮ ስለ ሕክምና ታሪኳ እንድትነጋገር እና ልዩ በሆነ ሁኔታዋ ላይ ተመሥርተውም ግላዊ ምክር ታገኝ ዘንድ አበረታቷት።
እርሷም የጤና አገልግሎት ምክረ ሐሳቡን በመቀበል ወደ ጤና ጣቢያ አምርታ ምርመራ አደረገች። በምርመራው እርግዝና እንዳልተፈጠረ አረጋገጠች፡፡ የወር አበባዋ መዛባት የተከሰተውም ጥንቃቄ የጎደለው የገብረ ሥጋ ግንኙነትን ተከትሎ በወሰደችው የወሊድ መከላከያ ምክንያት መኾኑን አወቀች፡፡ በየዕለቱ በኪኒን መልክ ስለሚወሰደው የእርግዝና መከላከያ መድኃኒት ተገቢውን ትምህርት ከወሰደች በኋላ ደግሞ የወር አበባ ዑደቷ መስተካከል ጀመረ። በሒደትም በሥነ ተዋልዶ ጤንነቷ ላይ አዎንታዊ ለውጦችን መመልከት ቻለች፡፡
ከተመለከተችው ለውጥ እና ካገኘችው አዲስ ግንዛቤ በመነሳትም፣ ምን ያህል የራስ መተማመኗን አዳብራ ሕይወቷን በተሳካ ሁኔታ መምራት እንደቻለች ታሪኳን ለማካፈል በከፍታ የወጣቶች ጤና አገልግሎትን ተገኝታ ምሥክርነት ሰጥታለች። አሁን ግለሰቧ፣ ሰዎች በሕይታቸው ላይ የሚወስኑትን ማንኛውም ውሣኔ በዕውቀት እና በማስተዋል መኾን እንደሚገባው ለዚህም እንደ ክፍታ ያሉ ፕሮጀክቶችን አስፈላጊነት አበክራ የምትናገር (የምታስተምር) እንስት ኾናለች፡፡
በርግጥም እንዲህ ያለው የስኬት ታሪክ የከፍታ እና ፕላን ኢንተርናሽናል ፕሮጀክቶች በትብብር ያሳኩት ተግባራዊ ሥራ ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የተቋማቱ ትብብር፣ ከፍታ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ሰራተኞች ላይ የሚያጋጥሟቸውን ወሳኝ የጤና እክሎች በተሳካ ሁኔታ ለመፍታት አስችሎታል፡፡
በተጨማሪም ወጣቶች እርስ በርስ እንዲቀራረቡ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ ከባቢን በመፍጠር ሰራተኞች በግልጽ እንዲነጋገሩ እና የጤና ችግሮቻቸውን እንዲፈቱም መደላድል ፈጥሮላቸዋል። የከፍታ የወጣቶች የጤና አገልግሎትም እንዲሁ ከፍ ብለን የተመለከትነውን ዐይነት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመሥጠት የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ጤናቸውን እንዲጠብቁ እና እንዲቆጣጠሩ በማስቻል፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ማህበረሰብ ውስጥ በጎ ለውጦች እንዲመጡ እና እንዲህ ያሉ ግንዛቤዎችም እንዲስፋፋ ምክንያት ኾኗል ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል።