የጤና ሚኒስቴር በጀርመን ግዙፍ የመድኃኒት አምራች ከሆነው ባየር ኤጂ መድሃኒት አምራች ኩባንያ ጋር በኢትዮጵያ የመድኃኒት ምርቶችን አቅርቦት ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ፤ ስምምነቱ በመላ አገሪቱ የመደሃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ለማገዝ እና አስፈላጊ መድሃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስች ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከባየር ጋር ያለው ስምምነት ጥራት ያላቸውን መድኃኒቶች አቅርቦት በማሻሻል ማህበረሰቦችን እንደሚጠቅም ተናግረዋል።
የመድኃኒት ዘርፉ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የምትፈልግባቸው ቁልፍ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዘርፍ የመንግስትና እና የግል ዘርፍ በመተባበር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የባየር ተወካይ እና የመድኃኒት ክፍል ኃላፊ ጆርጅ ሌቪንሰን ባየር በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በላይ ንቁ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን አዲሱ ስምምነት ስትሮክን ጨምሮ፣ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎችን እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን፣ እንዲሁም የእናቶች እና የህፃናት ጤና አገልግሎቶች ላይ የመድሃኒት አቅርቦትን በማሻሻል ላይ እንደሚያተኩር አመልክተዋል ተብሏል፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር የጀርመኑ ግዙፍ የፋርሚሲዩቲካል እና ባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባየር በኢትዮጵያ በመድኃኒት ማምረት ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁ ይታወሳል።
ኩባንያው ይህን ፍላጎቱን የተገለጸው የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን፣ ከባየር ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢል አንደርሰን ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።
ውይይቱ በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ባለው የመድኃኒት ዘርፍ ዙሪያ ባሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችና የትብብር አማራጮች ላይ ያተኮረ እንደነበር የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ አስታውቋል።
