የፌዴራል ህግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ዋነኛ ዓላማዎች መካከል አንዱ በሕግና ፍትህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊና ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማካሄድ በጥናት ግኝቶች መሠረት ለፖሊሲ እና ሕግ አዉጪዎች ምክረ ሀሳብ ማቅረብ በመሆኑ 75 የሚሆኑ ህገነክ ጥናቶችን መስራቱን ገለፀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ እንደተናገሩት የመንግሥት እና ሃይማኖት ግንኙነት በኢትዮጵያ፤ ትናንት፣ ዛሬና ነገ በሚል ርዕስ የጥናት ሥራም በኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ከተከናወኑ ጎላ ያሉ ጥናቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱን የጥናት ሥራዎችና ምክረ-ሐሳቦች መነሻ በማድረግ የተለያዩ የፖሊሲ ዉሳኔዎች እንዲሁም ሕጎች በሚመለከታቸዉ አካላት እንዲወጡ ሆኗል ያሉት ዳይሬክተሩ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነዉ ዐዉደ ጥበባዊ (Encyclopedic) አማርኛ-እንግሊዝኛ የሕግ መዝገበ ቃላት ሥራ ተከናዉኖ ታትሞ መሰራጨቱንም አክለዋል፡፡
በተጨማሪም የመጀመሪያው የተለያዩ የፌዴራል መንግሥቱን ሕጎች ለማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ ሕጎችን ለማውጣት የሚያግዙ የጥናት ሥራዎች ሲሆኑ በእነዚህ ጥናቶችም መነሻነት የተለያዩ ሕጎች እንዲሻሻሉ ወይም አዲስ ሕጎች እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በምሳሌነትም የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሕግና ተቋም መቋቋምያ፤ የአስተዳደር ሥርዓት ሕጎችን ጠቅሰዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም. የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ዘርፍ በራሱ የዉስጥ አቅም እንዲሁም ከዩኒቨርስቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ተቋማት ዉስጥ ከሚገኙ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር አምስት የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለዛሬዉ አዉደ ጥናት በኢትዮጵያ የአፍሪካ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ የሕግ ማዕቀፍ በሚል ርዕስ የሰራዉን ጥናት አቅርቧል ፡፡
