በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በፖለቲካዊ ጫና፣ በደህንነት ስጋቶች እየተፈተኑ ነው

Date:

በአለማችን ጋዜጠኞች ለከፍተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ሙያዊ ነፃነታቸው ተገፎ አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች ከሚፈጸምባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አንድ ጥናት አመላከተ፤ ከሙያቸው የሚጠበቅባቸውን ሥነ-ምግባር ለመተግበር እየተፈተኑ ነው ብሏል።


በጎርጎሮሳውያኑ 2023/24 የዓለም የጋዜጠኝነት ጥናት (WJS) አካል የሆኑ 363 ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ላይ በተደረገው ጥናት፣ 26.7 በመቶ የሚሆኑት ባለፉት አምስት ዓመታት በእስር ላይ እንደነበሩ ወይም ታስረው መፈታታቸውን ገልጸዋል። ተርየ ስካርዳል በተባለ ተመራማሪ የተዘጋጀውና የፎጆ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ባደረገው አዲስ ጥናት ይህ ውጤት በአለምአቀፉ ደረጃ አማካኝ ከሆነው የ3.7 በመቶ ጋር ሲነጻጸር በጣም የላቀ ነው ተብሏል።


በጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የክትትል እንቅስቃሴ መስተዋሉን የገለጸው ጥናቱ  ከጋዜጠኞቹ 46 በመቶ የሚሆኑት ክትትል እንደሚደረግባቸው እና 38.6በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የኢንተርኔት ድረ-ገጻቸው እና የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እንደተጠለፉ ወይም እንደታገዱ ተናግረዋል።


በግል ሚዲያዎች ላይ የሚስተዋለው የፆታዊ ትንኮሳም ከመንግስት መገናኛ ብዙኃን በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ እና አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል። በተጨማሪም “ኢትዮጵያ በደህንነት መለኪያዎች ስጋት ካለባቸው አምስት አገሮች አንዷ ሆና ተገኝታለች” ተብሏል።


በኢትዮጵያ ስላሉ ጋዜጠኞች የደህንነት ስጋት ያመለከተው ጥናቱ ከዓለም አቀፉ የሚዲያ ድጋፍ ድርጅት (IMS) የ2024 የጋዜጠኞች ደህንነት ግምገማ ሪፖርት ጋር የሚመሳሰል ነው። ሪፖርቱ በባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ቢያንስ 43 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን እና ለአፈና መዳረጋቸውን አመላክቷል።


በ60 ጋዜጠኞች ላይ በተደረገው ቃለ መጠይቅ ላይ የተመሠረተው ሪፖርቱ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተዋናዮች ላይ የሚፈጸሙ ዛቻዎች፣ እስር እና የትንኮሳ ድርጊቶች የመገናኛ ብዙኃን ደኅንነትን ስጋት ላይ ጥሏል ሲል አስጠንቅቋል። በአማራ፣በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልሎች ባሉ ግጭቶች ስር ሆነው የሚሰሩ ጋዜጠኞች ከፍተኛውን አደጋ እንደሚጋፈጡም ተረጋግጧል።


በቅርቡ ሶስት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ታፍነው መወሰዳቸውና መሰወራቸው ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል ተብሏል።


የፎጆ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ያጠናው ጥናት 363 የመንግሥት (የፌዴራል እና የክልል)፣ የግል፣ የማኅበረሰብ፣ የዓለም አቀፍ እና የፍሪላንስ ሚዲያ ባለሙያዎችን ተሳትፎ ባካተተ መልኩ የተካሄደ ሲሆን፣ በዜና አውታሮች ላይ ያለው ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል።


በተጨማሪም ከመንግሥትም ሆነ ከግል ሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ከመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስባቸው የጠቀሰው ጥናቱ፣ ኢትዮጵያ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከቱርክ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል።


በዜና አውታሮች ውስጥ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ እና የሚዲያ ተቋም ባለቤትነት አሁንም ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የቀጠሉ መሆናቸውን ጠቁሞ በግል የሚዲያ ተቋማት የሚሠሩ ጋዜጠኞች ከመንግሥት ሚዲያ ይልቅ በፖሊሲ መመሪያዎች ላይ ከፍተኛ ጥገኝነት እንዳላቸው ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ራስን ሳንሱር ማድረግም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል የተባለ ሲሆን፣ ፗ
ጥናቱ ኢትዮጵያን ጋዜጠኞች በውጫዊ ጫና ምክንያት ራሳቸውን ከሚገድቡባቸው አገሮች ተርታ አስቀምጧታል።


ጥናቱ የሙያ ሥነ-ምግባርን በተመለከተም፣ ጋዜጠኞች ሁልጊዜ ለሙያዊ ሕጎች መገዛት አለባቸው የሚለውን ሥነ-ምግባርን (absolutist ethics) የሚመርጡ ጋዜጠኞች ቁጥር መጨመሩን አረጋግጧል።


ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ የሙያ ሥነ-ምግባርን (situationist ethics) ማለትም የሙያ ሥነ-ምግባር እንደየሁኔታው መወሰን አለበት የሚለውን አስተሳሰብ በመደገፍ ከዓለም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብሏል። ይህም በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ያለበትን ገደብ አመላካች መሆኑ ተገልጿል።


በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እራሳቸውን እንደ መብት ተቆርቋሪ እና ተሟጋች ከማየት ይልቅ “ሀገር ገንቢዎች” እና “መፍትሄ አመላካቾች” እንደሆኑ  አድርገው ራሳቸውን ያቀርባሉ ያለው ጥናቱ ብሔራዊ ልማትን መደገፍ፣ ሰላምና መቻቻልን መስበክ እና መፍትሄዎችን መጠቆም በስልጣን ላይ ያሉትን ከመመርመር የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ ብሏል።


በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ያለው መንግስትን የመቆጣጠር እና ስለመብት የመሞገት አዝማሚያ ደካማ ነው ተብሎ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን እንደ አዲስ ስታንዳርድ እና መቐለ ኤፍ ኤም 104.4 ያሉ ሚዲያዎች በአንጻሩ ስልጣን ላይ ያሉትን የመከታተል ተግባር ላይ የበለጠ ትኩረት እንደሰጡ በጥናቱ ተለይተው ተጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል እንደ ኢትዮጵያ ሄራልድ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያሉ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ፖሊሲዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ቅድሚያ እንደሚሰጡ አመልክቷል።


በአጠቃላይ፣ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ለከባድ የደህንነት ስጋት፣ ለተገደበ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትና ለከፍተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቅሶ ከወሳኝ የምርመራ ስራዎች ይልቅ ወደ ልማት ያደላ ሚናን እያመጣጠኑ እንደሚሰሩ ጠቁሟል። አስ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...

የአህጉሪቱን የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 250 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቀደ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ...

በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም

አሜሪካ እና ኢራን በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ...

እስራኤል ጦሯ በደቡብ ሊባኖስ እንደሚቆይ አስታወቀች

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እንደተናገሩት፤ በአሜሪካ እና በኢራን...