ጥበባት ለሀገር ማንነት እና እድገት ቁልፍ ናቸው ባሕላዊ ሀብትን ጠብቀው ያቆያሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጥበባት ለማኅበራዊ አንድነት አበክረው በመስራትም ብዝኃነት ላላቸው ማኅበረሰቦች ድምፅ ይሆናሉ ብለዋል።
በትምህርት ረገድም ጥበባት ፈጠራን እና ምክንያታዊ አስተሳሰብን ያሳድጋሉ። በኢኮኖሚ ረገድም ጥበባት ፈጠራን፣ ቱሪዝምን እና ስራ ፈጠራን የመምራት አቅምም አላቸው ሲሉም ገልጸዋል።
ትላንት ጠዋት ከመላው ኢትዮጵያ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከተወጣጡ የጥበቡ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ማካሔዳቸውን ገልጸዋል።
ተወካዮቹ በተለያየ ደረጃ እየተካሄደ በመጣውና በዘርፉ ያሉ ቁልፍ ጉዳዮችን ለመለየት በረዳው ሰፊ የውይይት መርሃ-ግብር የተሳተፉ ናቸው ብለዋል።
መድረኩም የውይይት ግኝቶቹን በማጠናከር የከፍተኛ አመራሩን ትኩረት እና መፍትሔ የሚሹ እንዲሁም በዚህ መስክ የተሰማሩ አካላት ሚናቸውን የሚወጡባቸው ጉዳዮችን በመለየት ላይ ያተኮረ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።