ፖሊስ 47 የጤና ባለሙያዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን አስታወቀ

Date:


ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ “በሀገሪቱ ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር በማበር ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፣ በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል የተጠረጠሩ” 47 የጤና ባለሙያዎችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

እነዚህ ተጠርጣሪዎች የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ እንደሽፋን በመጠቀም ሕገ-ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፤ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ለአድማ በማነሳሰት፣ የታካሚዎች ሕይወት ለሞትና ለአደጋ እንዲጋለጥ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የተጠረጠሩ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ የጤና ተቋማት የአድማ መረቦችን በመዘርጋት፤ የጤና ባለሙያ ያልሆኑ አካላትን ነጭ ጋዋን በማስለበስ የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተው ሁከት እንዲፈጥሩ በማድረግ፣ ያልተገባ ወሬ በመንዛት እና በተለያየ መንገድ ሰላማዊ የሕክምና ሂደትን በማደናቀፍ የሕሙማንና የጤና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ፣ በመንግሥት የሕክምና አገልግሎት እና ትምህርት በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል ማድረጋቸውንም የፌደራል ፖሊስ ወቅታዊ መረጃን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

እንዲሁም ሙያቸውን አክብረው በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት ከማድረስ ባለፈ ሁከት እንዲፈጠር ሙከራዎችን አድርገዋል ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎች በመረጃና በማስረጃ በመለየት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጤና ባለሙያዎቹ የሙያው ሥነ-ምግባርና ሕግ በማይፈቅደው ሁኔታ የዜጎችን ሕይወት ለሞትና ለአደጋ በማጋለጥ ሥራ ማቆም፣ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ማነሳሳት እና ማስፈራራት የወንጀል ተግባር መሆኑን የገለጸም ሲሆን፤ ሌሎችም ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

የፌደራል ፖሊስ ሕዝባቸውን እና ሕግ አክብረው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ ያረጋገጠም ሲሆን፤ ከዚህ ውጭ ሁከትና ብጥብጥን ለማስፋፋት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስ እየወሰደ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...