ከ”ከነዓን የስፖርት ትጥቅ አምራች” ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የቦሌ ክፍለ ከተማ የ2018 የበጋ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር በድምቀት ተጀመረ።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ከክፍለ ከተማው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ”ከነዓን የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት” ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 4ኛው ዙር የበጋ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ወረዳ 5 በሚገኘው “24 ሜዳ” ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ስፖርተኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በባለፈው ቅዳሜ የካቲት28/2018 ዓ.ም በድምቀት ተጀምሯል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አደፍርስ ኮራ ውድድሩን በይፋ ሲያስጀምሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ስፖርት ለጤናማና አምራች ትውልድ ግንባታ ያለውን ፋይዳ ገልጸዋል።
ከለውጡ ማግስት በፌዴራል መንግስትና የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጡትን ልዩ ትኩረት ተከትሎ በክፍለ ከተማ ደረጃም ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ አደፍርስ አክለውም “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለስፖርት መሠረተ ልማትና ለወጣቶች አቅም ግንባታ የሰጡት ትልቅ ራዕይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ የአዲስ አበባን ስፖርታዊ ገጽታ ለመለወጥና ዘመናዊ የስፓርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለታዳጊዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ለዛሬው ውድድር መሳካት ትልቁን ድርሻ ይይዛል” ብለዋል።
የክፍለ ከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳግም ጣሰው በበኩላቸው ውድድሩ ከ”ከነዓን የስፖርት ትጥቅ አምራች” ጋር በመተባበር መዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ ይህም የግል ዘርፉ ለስፖርቱ ዕድገት ያለውን አጋርነት ያሳየበት ነው ብለዋል። ውድድሩ ታዳጊዎች ከመጥፎ ነገሮች ርቀው በስፖርት የታነጹ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የታደሙት የቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ መሰል የታዳጊዎች ውድድር ለሀገራችን ብሔራዊ ቡድንና ለክለቦች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት መሰረት መሆናቸውን ገልጸው፤ የክፍለ ከተማው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር በሦስት የዕድሜ እርከኖች (ከ13፣ 15 እና 17 ዓመት በታች) የተዋቀሩ 44 ቡድኖችንና ከ1,000 በላይ ታዳጊዎችን የሚያሳትፍ ሲሆን፣ እስከ ግንቦት 15 ቀን 2018 ለሁለት ወራት እንደሚቀጥል በማስጀመሪያው ተመላክቷል።
በተያያዘ መረጃ መሰረት ለታዳጊ ፕሮጀክቶች ለጤና ቡድኖችለተለያዩ የስፖርት ቡድኖች የስፖርት ትጥቅ አምራችናአቅራቢ የሆነዉ
“ከነዓን የስፖርት ትጥቅ አምራች” ድርጅት በተተኪው ትዉልድ ላይ አሻራውን እያሳረፈ የሚገኝ ሲሆን 4ኛዉን የበጋ ታዳጊ የእግርኳስ ዉድድርን በዋና ደጋፊነት ከቦሌ ክፍለከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከቦሌ ክፍለከተማ የእግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር ተዘጋጅቷል።
ከነዓን የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ላለፉት 3 ዓመታት ከ600 በላይ የስፖርት ቡድኖች ክለቦችን ጥራትና በተፈላጊ ምርቶቹ ተደራሽነቱን እያረጋገጠ የሚገኝ ሲሆን ለአገራችን ስፖርት ደማቅ አሻራ ማስቀመጥን ዓላማዉ ማድረጉን የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከነዓን ሰሎሞን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከነዓን የስፖርት ትጥቅ አምራች ከቦሌ ክ/ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ፅ/ቤት ከቦሌ ክ/ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ የ2018ዓ.ም.የበጋ የታዳጊ ወጣቶችን የእግር ኳስ ዉድድር በትብብር ከማዘጋጀታቸዉ በተጨማሪም በዉድድሩ ከፍተኛ ተሰጥኦ ለሚያሳዩና ለአሸናፊዎች የተለያዩ የማበረቻና ሽልማት ለመስጠት የተነገረ ሲሆን ወደፊትም በስፖርቱ ዘርፍ ይበልጥ በመስራት ደማቅ አሻራውን ለማስቀመጥ እንዳለመ ተብራርቷል።
ቅዳሜ የካቲት 28/2018 ዓ.ም በቦሌ ክፍለከተማ የ2018 ዓም.የበጋ የታዳጊዎች የእግርኳስ ዉድድር በተጀመረው 44 ቡድኖች ከ1000 በላይ ታዳጊዎችና ተሳታፊዎች እንዲሁም በርካታ ዳኞች የሚሳተፉበት ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ለምታደርገው ጥረት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትታምኖበታል።ሁሉም የከተማዋና የክፍለከተማዉ ነዋሪዎች በስፖርት ሜዳዉ በመገኘት መታደም መደገፍ እንደሚቻል ጥሪ ተደርጓል።
ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሲሳይ መንግስቴ
