ሜላት ሚካኤል (ሞዴሊስትና ዲዛይነር)
ሜላት ሚካኤል ትባላለች፡፡ የሀገራችንን የፋሽን ኢንዱስትሪ ወደ ዓለም መድረክ ለማውጣት እየሠራ ያለ ‹‹Melly Fashion›› የተሰኘውን ተቋም መሥራችና ባለቤት ነች፡፡ በእርግጥ ሜላት በአንድ ሙያ ብቻ የምትጠራ አይደለችም፡፡ የፋሽን አልባሳት ዲዛይነር ብትሆንም ቴክኖሎጂው፣ አስተማሪነቱ፣ ኤቨንት ኦርጋናይዝ እና ንግዱ ውስጥም አለችበት፡፡
ሜላት በ‹‹Melly Fashion›› በኩል በቅርቡ አንድ ትልቅ መድረክ አዘጋጅታ ነበር፡፡ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ‹‹Melly Fashion, Addis Fashion week” የሚል ስያሜ ተሠጥቶት የተዘጋጀው ፕሮግራም እጅግ ሰፊና ታላቅ ራዕይን ያነገበ ሲሆን፣ ይህንን መነሻ በማድረግም የግዮን ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ከሜላት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ በቆይታቸውም ስለብዙ ሌሎች ጉዳዮች አንስተዋል፡፡ ሁሉንም ከቀጣዩ ቃለ ምልልስ ታገኙታላችሁ፡፡ መልካም ቆይታ፡፡
ግዮን፡- ቆይታችንን ራስሽን በማስተዋወቅ ብንጀምር? …ሜላት ማንናት?
ሜላት፡- በዐጭሩ ለመግለፅ የተወለድኩት አዲስ አበባ፣ ያደኩት ደግሞ ድሬዳዋ ነው፡፡ ከድሬዳዋ በኋላ ወደ ቻይና አቅንቼ እዚያ ለ15 ዓመታት ኖሬያለሁ፡፡ ከሥራ ጋር የተዋወኩት ማለትም ሥራ የጀመርኩትም በቻይና ነው፡፡
ግዮን፡- ላለፉት ረዘም ያሉ ዓመታት በሞዴሊንግ ሙያ ስትሰሪ መቆየትሽ ይታወቃልና እስቲ ስለሙያ አጀማመርሽ ንገሪኝ?
ሜላት፡- የሙያው አጀማመሬ ከልጅነት ዕድሜዬ ጋር ይያያዛል፡፡ ልጅ ሆኜ ጀምሮ ልብስ በጣም ነው የምወደው፡፡ ወላጅ እናቴም ለልብስ የተለየ ነገር ስላላት አዳዲስ ፋሽን ልብሶችን ዲዛይን ታደርግ ነበር፡፡ ት/ቤት ደግሞ በክበባት ውስጥ በተለይም ከኪነጥበብ ጋር በተያያዘ ንቁ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው ወደ ሞዴሊንግ ሙያ እንድሳብ ያደረገኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡
ግዮን፡- በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ መሳተፍ የጀመርሽው መቼ ነው?
ሜላት፡- ከኮቪድ በፊት በነበሩት ጊዜያት በኢንተርቴመንት ፕሮግራሞች ላይ ነበር የምሳተፈው፡፡ ከፋሽን ሾው ጋር በተያያዘ ሞዴሎችን የማሰልጠን፣ መድረክ የማመቻቸት ዓይነት ሥራዎችን ነበር የምሠራው፡፡ በአንዳንዶቹ መድረኮች ደግሞ ራሴም በሞዴልነት እሳተፍ ነበር፡፡ ኮቪድ ከመጣ በኋላ ደግሞ ወደ ዲዛይነርነቱ ነው ያዘነበልኩት፡፡ ባለፉት 5 ዓመታትም ይህንኑ አጠንክሬ ቀጥያለሁ፡፡
ግዮን፡- እንግዲህ ዛሬ ተገናኝተን ይህን ቆይታ እንድናደርግ ምክንያት የሆነን በቅርቡ በአዲስ አበባ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል አዘጋጅተሸው የነበረው የፋሽን ሳምንት ፕሮግራም ነው፡፡ ይህን ፕሮግራም ለማዘጋጀት ካነሳሳሽ ጉዳይ ጀምረሽ፣ ስለ ፕሮግራሙ አጠቃላይ ሁኔታ ብትነግሪን?
ሜላት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የፋሽን ባለሙያዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እኔ ግን የውጪው ዓለም ልምድ አለኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ከመዘንነው ኢትዮጵያ ያሉ ባለሙያዎች ጋር የተወሰነ ጉድለት አያለሁ፡፡ ከመድረኩ (stage) ጀምሮ ዲዛይኖችን ዓለም ዓቀፋዊ ይዘት እንዲኖራቸው እስከማድረግ ድረስ የሚቀራቸው ነገር አለ፡፡ ዲዛይነሮቹ ሲሰሩት ለእኛ ብቻ አድርገው ነው፡፡ ብዙው የውጪው ዓለም ዜጋ ግን የእኛን መልበስ ቢፈልግም እንደሚፈልገው አያገኝም፡፡ ሌላው ብዙዎች ዲዛይነሮች ሽመና ላይ የተንተራሱ ናቸው፡፡ የሽመናን ልብስ የዓለም ገበያ ላይ በውድ መሸጥ ደግሞ ከባድ ነው፡፡ እኔም ይሄን ነገር እንዴት ማስተካከል ይቻላል? ልብሳችንን እንዴት አስወድደን መሸጥ እንችላለን? ከሚል በመነሳት የራሴን ብራንድ ልብሶች ለሌላው በተምሳሌትነት ለማቅረብ በመፈለጌና ችግሩን ከገበያው ዕድል ጋር እንዴት ማስታረቅ እንደምንችል ለማሳየት በማሰብ ነው ፕሮግራሙን ያዘጋጀሁት፡፡
ግዮን፡- እና እንዳሰብሽው ሆኖልሻል?
ሜላት፡- በእርግጥ ፕሮግራሙ ላይ ትንሽ የማኔጅመንት ችግር ነበር፡፡ ፕሮግራሜን እንደማንኛውም የእለቱ እንግዳ ‹‹እንግዳ›› ሆኜ ተቀምጬ ለማየት ነበር ሃሳቤ፤ ግን አልሆነም፡፡ ሙሉ ፕሮግራሙን ራሴ ነበርኩ ሳስቀጥል የነበርኩት፡፡ የመጀመሪያ ፕሮግራም በመሆኑ ግን ይሄ የሚያጋጥም ነው፡፡ በተረፈ የፋሽን ሾው ትርዒቱ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር፤ ልብሶቹም በጣም ተወደውልኛል፡፡
ግዮን፡- የዝግጅትሽ ስያሜ ‹‹የፋሽን ሳምንት›› ነበር የሚለው፡፡ የተካሄደው ግን አንድ ቀን ብቻ ነው፡፡ ከዝግጅቱ አንፃር ሥያሜው ትንሽ አልተጋነነም?
ሜላት፡- ልክ ነህ፡፡ ‹‹የፋሽን ሳምንት›› ተብሎ ለአንድ ቀን ነው የተካሄደው፡፡ ነገር ግን ይሄ ፕሮግራም በቀጣይ የምንሠራው ትልቅ መድረክ መክፈቻ ነው፡፡ ከሦስት ወር በኋላ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም የኢትዮጵያ ዲዛይነሮች በብዛት የሚሳተፉበትን የፋሽን ሳምንት እናዘጋጃለን፡፡ ይሄም ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡ የብዙኃን ዲዛይነሮች ፈጠራዎች የሚቀርቡበት ሰፋ ያለ የፋሽን ሳምንት በተከታታይ ይኖረናል፡፡ ይሄ ነገር በሌላው ዓለም የተለመደ እና ለብዙ ዓመታት እየተሠራበት ያለ ነው፡፡ በእኛ ሀገር ግን አልተለመደም፤ ለዚህ ነው የአሁኑ ፕሮግራም መክፈቻም ቢሆን የቀጣዮቹን ተከታታይ ዝግጅቶች ሥያሜ እንዲይዝ የተደረገው፡፡
ግዮን፡- በመክፈቻውም ቢሆን ሌሎች ዲዛይነሮችን ማሳተፍ አይቻልም ነበር?
ሜላት፡- እኔ እዚህ ሀገር ምንም ዓይነት ሥራ ሰርቼ ስለማላውቅ እነማን የት እንዳሉ ለማወቅ ይቸግረኛል፡፡ ከዚያ ይልቅ አንዴ የራሴን አዘጋጅቼ በተቻለ መጠን ብዙዎች ተገኝተው እንዲያዩልኝ በማድረግ በዚያው ብተዋወቃቸውና ቀጣይ ፕሮግራሜን ባስተዋውቅ የተሻለ ስለመሠለኝ ነው መክፈቻውን በእኔ ብራንድ ብቻ ያደረኩት፡፡ በእርግጥም ይሄ ሐሳቤ ተሳክቷል ማለት እችላለሁ፡፡ አብዛኛዎቹም ዓላማዬን በመደገፍ አብረውኝ እንደሚሠሩ ቃል ገብተውልኛል፡፡
ግዮን፡- ከዚህ በኋላ በየሦስት ወሩ ለማዘጋጀት ነው ያሰባችሁት?
ሜላት፡- በየሦስት ወሩ ሳይሆን በዓመት ሁለት ጊዜ በየ6 ወሩ ለማድረግ ነው ያቀድነው፡፡ የአሁኑን እንደመክፈቻ ቆጥረን ከሚቀጥለው (ከ3 ወር በኋላ ከምናዘጋጀው) የፋሽን ሳምንት ጀምሮ በየስድስት ወሩ በቋሚነት እናዘጋጃለን፡፡
ግዮን፡- ለሀገሩ በተለይም ከሞያው አንፃር እንግዳ እንደመሆንሽ ብራንድ ልብሶችሽን የሚያሳዩልሽን ሞዴሎች ለማግኘት አልተቸገርሽም?
ሜላት፡- ከባድ ነበር፤ ግን ተወጥቼዋለሁ፡፡ ሞዴሎቹ በዓለም አቀፍ መመዘኛ መሠረት ከ1.75 ሜትር በላይ እንዲሆኑ ፈልጌ የነበረ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ማሳካት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ እስከ 1.72 የነበሩትንም በደንብ ስልጠና በመስጠት አሳትፌያለሁ፡፡
ግዮን፡- በእኛ ሀገር ሞዴሊንግ የሚወደድ ሙያ ቢሆንም ከሥልጠና ወይም ሙያውን አውቆ ከመሥራት አንጻር ትንሽ የማይባል ክፍተት አለ፡፡ አንቺ ይኼን ነገር አልታዘብሽም?
ሜላት፡- ሞዴሎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ባለሙያዎችም የክህሎት ችግር እንዳለባቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ከዲኮር ጀምሮ እስከ መድረክ መሪዎችና ኬሮግራፈሮች ድረስ ብዙ የሚቀራቸው ነገር አለ፡፡ ምናልባት ባለሙያዎቹ እዚህ ሀገር ላለው ወይም ለተለመደው አሠራር ከበቂ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በውጪ ሀገራት ካለው ጋር ካነፃፀርነው ግን በጣም ከባድ ክፍተት ነው ያለው፡፡ በበኩሌ በቀጣይ ዝግጅቶቼ ባለሙያዎችን ከውጪ ሀገር ማስመጣት እንዳለብኝ አምኛለሁ፡፡ ወደ ጥያቄው ስመለስ… ያው አብዛኛዎቹ ሞዴሎች በተፈጥሮ ተክለ ቁመና ሙያውን የሚመጥን አቋም የታደሉ ቢሆንም ሙያው ከሚፈልገው ተጨማሪ ክህሎት አንፃር ሙሉ እና ብቁ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ ብዙዎቹን ፍላጎቱ እንጂ ችሎታው ኖሯቸው አላገኘኋቸውም፡፡ ለዚህ ነው እንደ አዲስ ማሰልጠን እንዳለብኝ አምኜ ይህን ሳደርግ የነበረው፡፡ አረማመድ (walking) ላይ ችግር አለ፡፡ አብዛኞቹ አንድ ዐይነት አረማመድ ነው የሚያውቁት፡፡ የካትዎክ አጠባበቅ፣ ጓደኛን የማየት፣ ወዘተ… ብዙ ዓይነት ችግር ነበረባቸው፡፡ ይሄን ለማስተካከል ሞዴሎች ላይ ብዙ ሥራ ሠርቻለሁ፡፡
በርግጥ ይሄ ችግር ከማኅበረሰቡ አመለካከትም ጋር የተያያዘ እንዲሆነ ይገባኛል፡፡ ሞዴሊንግ የትርፍ ሰዓት ሥራ እንጂ እንደሙያ አልተያዘም፡፡ ቤተሰብም ቢሆን እንደሙያ ስለማይቆጥረው ልጆቹን በዚህ መንገድ እንዲሄዱ አይፈቅድም፡፡ ‹‹ብትማር/ብትማሪ ይሻላል፤ ጊዜህን/ጊዜሽን አታጥፊ›› የሚል ዓይነት ወቀሳና ትችት ይበዛል፡፡ ሙያው ግን እጅግ የተከበረና ልዩ ትኩረት የሚሠጠው ነው፡፡ ከምግብ አንፃር እንኳን ሞዴሎች የየራሳቸው የምግብ ሥርዓት አላቸው፡፡ ምን መመገብ፣ የትኛውን የሰውነት አካል መጠበቅ እንዳለባቸው ራሱን የቻለ በሳይንስ የተደገፈ ዝርዝር ነገሮች አሉ፡፡
ግዮን፡- ታዲያ ይሄን ነገር ስለመቀየር አላሰብሽም?
ሜላት፡- ወደፊት በዚህ ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ በጣም ብዙ ዐቅም ያላቸው ልጆች እንዳሉ ስለገባኝ እነርሱን አሠልጥኖ ወደ ዓለም አቀፍ ‹‹ቶፕ ሞዴልነት›› ለማሻገር ሰፊ ሥራ እሠራለሁ፡፡
ግዮን፡- ‹‹የፋሽን ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ትርዒት›› የሚለው የዝግጅትሽ ተጨማሪ ሥያሜ ፋሽንና ቴክኖሎጂን አዋሕዶ የመሥራት ዓላማ እንዳለው ይነግረናል፡፡ ሁለቱን በአንድ ላይ ያመጣሽበት ምክንያት ምንድነው?
ሜላት፡- ፋሽንና ቴክኖሎጂ በእኔ ሕይወት ውስጥ የየራሳቸው ቦታ አላቸው፡፡ ሌላ የቴክኖሎጂ ካምፓኒም አለኝ፡፡ ‹‹ቺቫ›› ይባላል፤ አፕሊኬሽን ነው የሚሠራው፡፡ ከትንሽ ወራት በኋላም አስመርቀዋለሁ፡፡ ሕይወትን ቀላል ለማድረግ የሚሠራ ነው፡፡ ይህን ካምፓኒ ማስተዋወቅ ስለምፈልግ ነው ከፋሽኑ ጋር ያመጣሁት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፋሽንና ቴክኖሎጂ የሚገናኙበት ሁኔታ አለ፡፡ የፋሽን ዝግጅቱን ስናዘጋጅ ከመጥሪያው ጀምሮ የነበረው ነገር ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ ነበር፡፡ የብራንድ ልብሶቹ ሽያጭም በዌብሳይታችን በኩል የሚከናወን ነው፡፡ የወንድ፣ የሴት፣ የልጅ፣ የአዋቂ ልብሶችን ሁሉ ማንም ሰው መርጦ የሚገዛበት ዌብሳይት ነው ያለን፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች አንጻር ነው ፋሽንና ቴክኖሎጂን አያይዤ የመጣሁት፡፡
ግዮን፡- ሁላችንም እንደምንረዳው የዲዛይን ሙያ (ተሰጥኦ) በትምህርት ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በተፈጥሮ መታደልንም ይፈልጋል፡፡ በተፈጥሮ የታደሉ፣ ነገር ግን ቀዳዳውን ያላገኙ በርካታ ወገኖቻችንም በየቤታቸው ተቀምጠው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያሰብሽው ነገር የለም?
ሜላት፡- ደስ የሚል ጥያቄ አነሳህ፡፡ ይሄ ነገር ለብዙ ጊዜ ሲያብሰለስለኝ የቆየ ነው፡፡ እኔ በአሁኑ ጊዜ በቅድሚያ ዕድል እየሠጠሁ ያለሁት ቤታቸው ቁጭ ላሉ፣ ችሎታው ኖሯቸው የመተግበሪያ አቅም ላጡና የገንዘብ ድጋፍ ለሌላቸው ልጆች ነው፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት የዲዛይን ችሎታ ኖሯቸው አቅም ያጡ ዜጎችን አግዛለሁ፡፡ እነዚህን ሰብስበን የተፈጥሮ ችሎታቸውን እንዲያወጡት እናደርጋለን፡፡ ከሥልጠና ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የሚወጡበትን ዕድል እንፈጥራለን፡፡
ግዮን፡- ‹‹ሜሊ ፋሽን›› ብራንድ አልባሳቱን የሚያመርትበት ዋና መሥሪያ ቤቱ የት ነው? ቅርጫፎችስ አሉት?
ሜላት፡- ዋናው ማምረቻና መደብር ያለው ቻይና ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ቅርንጫፎች አለው፡፡ 22 ማዞሪያ አካባቢ ነው የሚገኘው፡፡ ሽያጩ በአብዛኛው በኦንላይን የሚከናወን በመሆኑ ግን በመላው ዓለም አለን ማለት እንችላለን፡፡
ግዮን፦ ቻይና ውስጥ የፋሸን ሾው አዘጋጅተሽ ታውቂያለሽ?
ሜላት፡- እኛ ብዙውን ጊዜ የኤቨንት አዘጋጆች ሆነን ነው የሠራነው፡፡ የሻንጃን ፋሽን ዊክ እና ሌሎችንም በርካታ መድረኮች ያዘጋጀነው እኛ ነን፡፡ ነገር ግን የራሴን ብራንድ ብቻ በቻይና ያቀረብኩበት መድረክ የለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ኤቨንት ላይ ነው ስንሠራ የነበረው፡፡ ዝነኞችን ማምጣት፣ ዘፋኞችን ከሌላ ዓለም ጋብዞ ኮንሠርት ማዘጋጀት፣… የመሳሰሉ ኤቨነቶችን እንሠራለን፡፡ከዚህ ቀደም እንደ አሸር፣ ፒትፑል፣ ቲፔይን፣ ሲያራ፣… የመሣሠሉትንና ሌሎች ታዋቂ ዲጂዎችንም አስመጥተን ትልልቅ ኮንሠርቶችን አዘጋጅተናል፡፡ ወደፊት ደግሞ አሁን በአገር ቤት የጀመርነውን ቻይና ውስጥ እንቀጥለዋለን፡፡
ግዮን፡- አሁን በዋናነት እየሠራሻቸው ያሉ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?
ሜላት፡- እኔ እንግዲህ ቻይና ውስጥም እዚህም በዋናነት የምሠራው የተለያዩ ነገር ግን ተመጋጋቢ የሆኑ ሙያዎችን ነው፡፡ እኔ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ነኝ፡፡ ስቴት ማናጀር ነኝ፤ ፋሽን ዲዛይነር ነኝ፤ሞዴሊንግ አሰልጣኝ ነኝ፤ አስተማሪ ነኝ፡፡ ሰው እንዴት ነው ‹‹ሱፐር ስታር›› መሆን የሚችለው? በሚለው ላይ እየተጋበዝኩ ሥልጠና እሠጣለሁ፤ ፕሮሞተርም ነኝ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ወደ ቢዝነሱ ያደላሁ ይመስለኛል፡፡ በቴክኖሎጂ ካምፓኒዬ በኩል ሰዎች በቀላሉ ሸመታቸውን ማከናወን የሚችሉበት ላይ በማተኮር እዚህ ቢዝነስ ወስጥ ይበልጥ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ ይሄ በርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የንግድ ባሕል አስገዳጅነት የገባሁበት ነው፡፡ ምክንያቱም እዚህ ሀገር ካሽ ካልተያዘ ሥራ መሥራት ከባድ ነው፡፡ ቻይና ውስጥ የትኛውንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት ፍላጎትና ሐሳብ እንጂ ካሽ ያን ያህል አስገዳጅ ላይሆን ይችላል፡፡ እዚህ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ምንም ነገር ለማድረግ ካሽ ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ለመያዝ ቢዝነሱን ጠበቅ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ውስጥ የኢምፖርት ኤክስፖርት ቢዝነስንም እሠራለሁ፡፡ የ‹‹ኢንዱስትሪያል ሚኒራል›› ግብአቶችን የመላክ እና የማስመጣት ሥራ አለኝ፡፡ ሆቢዬ የሆነውን የፋሽን ሙያ ለመከወን የቢዝነስ ሴክተሩ ሥራዬ ዋናውን አቅም የማጎልበት ሚና የሚጫወትልኝ ነው፡፡
ግዮን፡- የብራንድ አምባሳደርሽን የመረጥሻት በምን መሥፈርት ነው? ለዚህ የሚሆኑ የሀገር ልጆች አጥተሸ ነው?
ሜላት፡- ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ነው፡፡ እንዳልከው የእኔ ብራንድ አምባሳደር ነጭ ናት፡፡ ነገር ግን ሙያው የሚፈልገውን ሁሉ የምታሟላ ፕሮፌሽናል ባለሙያ ነች፡፡ እዚህ ድረስ አምጥቼ ያስፈረምኳትም ለብዙኀን ትምህርት እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡ ይህቺ ብራንድ አምባሳደራችን በተፈጥሮ ካላት ውበት በተጨማሪ ሙያው የሚፈልገውን ነገር በመጠበቅ በኩል አንድም እንከን የለባትም፡፡ ምግቧን መጥና እና ሳይንሱ የሚለውን ለክታና መርጣ የምትመገብ፣ የሚገባትን ኤክሰርሳይስ የምትሠራ፣ ለሰውነቷ የሚያስፈልጋትን ቫይታሚን፣ ሚንራል፣ ካሎሪ፣… በአግባቡ የምትወስድ በጣም ጎበዝ ሞዴል ነች፡፡ ለዚህ ነው ብራንድ አምባሳደር ያደረግናት፡፡
ግዮን፡- ይህን ሁሉ የምታሟላ የሀገራችን ሞዴል የለችም?
ሜላት፡- ልትኖር ትችላለች፣ እኔ ግን አላገኘኋትም፡፡ ምናልባት ወደፊት በሚኖረን የተሻለ ግንኙነትና በእኛም የሥልጠና ሂደት ለሙያው የታመኑ ሞዴሎችን ካወጣን፣ ያኔ የእኛን ልጆች አወዳድረን በብራንድ አምባሳደርነት እንሾማለን፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻም ምን መናገር ትፈልጊያለሽ?
ሜላት፡- ከሁሉ በፊት እግዚአብሔርን አመሠግናለሁ፡፡ እኔ ይህን ሥራ እየሠራሁ ያለሁት በራሴ የገንዘብ አቅም ነው፡፡ የሀገራችንን ሞዴሎችና ዲዛይነሮች ወደ ዐለም መድረክ ለማውጣት አስቤ እየሠራሁ ያለሁት በራሴ ገንዘብ ነው፡፡ ወጪው የብቻዬ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን ለሀገር የሚጠቅም እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ ስለዚህ ዓላማና ራዕዬ የገባቸው ሰዎች በየትኛውም መልኩ ቢያግዙኝ ደስ ይለኛል፡፡ በርግጥ ጓደኞቼና የቢሮ ሠራተኞቼ ፕሮግራማችንን ለማሳካት ብዙ ለፍተዋል፤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በተረፈ ሥራዬን አይታችሁ እኔን ለማበረታታትና ለማስተዋወቅ ለወደዳችሁ የግዮን መጽሔት አዘጋጆች በሙሉ የከበረ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ግዮን፡- እኛም በእጅጉ እናመሠግናለን፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 220 ታህሳስ 12 2017 ዓ.ም