የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የጥቅምት ወር ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ምክንያት በማድረግ ለ100 ሴቶች ነፃ የጡት እና የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቋል ።
ሆስፒታሉ ይህንን ያስታወቀው ጥቅምት 20 ቀን 2019 ዓ.ም ላይ ከየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ጋር በመተባበር የጡት እና የማህፀን በር ካንሰር በሽታን መከላከልን አስመልክቶ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ባከናወነበት ወቅት ነው ።
የሆስፒታሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የአካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ስንታየሁ ድንቁ እንደገለፁት፡ ሆስፒታሉ ለአንድ ቀን ብቻ ነፃ የምርመራ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ።
ሆስፒታሉ ለአንድ ቀን ብቻ በሚሰጠው ነፃ ምርመራ ለ100 ሴቶች ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ዕድል ቢፈጥርም በግንዛቤ እጥረት ችግር ምክንያት ምርመራ እያደረጉ ያሉት ውስን መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ሆስፒታሉ ይህንን አገልግሎት እየሰጠ ያለው ከየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ጋር በመሆን እንደሆነ የገለፁት ስራ አስፈፃሚዋ በቀጣይ በጡት እና በማህፀን በር ካንሰር ላይ ያለውን የግንዛቤ እጥረት ለመፍታት ወጥነት ያለው አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል ።
በተለይም የችግሩን አስከፊነት በመረዳት ማህበረሰቡ አከባቢው ቀረብ ባለ ሆስፒታል በመሄድና ምርመራ በማድረግ የጡት ሆነ የማህፀን በር ካንሰርን ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ ጠቁመዋል ።
(አሐዱ ሬድዮ)
