ከውጭ ተቋራጮች ጥገኝነት ወጥቶ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶችና ባለሙያዎች አቅም የሚመራው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር፣ ከኪሳራ ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩ በአገሪቱ የመሠረተ ልማት ዘርፍ አበረታች ምዕራፍ ሆኗል።
ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዘላቂ ውጤት እንዲያስገኙ፣ ከግንባታ በኋላ በራስ አቅም ማስተዳደር፣ መጠገንና ማሳደግ ወሳኝ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ያሳየው ለውጥ የኢትዮጵያውያንን የምህንድስና፣ የቴክኒክና የአስተዳደር ብቃት በተግባር ያሳየ ስኬት ነው።
ቀደም ሲል በከፍተኛ የፋይናንስ ጫና፣ በውጭ ተቋራጮች የአስተዳደር ክፍያና በመስመሩ ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች ምክንያት የኪሳራ አዙሪት ውስጥ የነበረው ተቋሙ፣ በአስተዳደር ለውጥ፣ በውስጥ ሪፎርምና በሰው ኃይል አቅም ማጠናከር ወደ ትርፋማነት ተሸጋግሯል።
የለውጡ መሠረታዊ ምዕራፍ የተጀመረው ግንቦት 2016 ዓ.ም የ756 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር አስተዳደርና የጥገና ቁጥጥር በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንዲመራ ከተደረገ በኋላ ነው። ይህም ከውጭ ጥገኝነት ለመውጣትና የአገር ውስጥ የሙያ እውቀትን ወደ ተግባራዊ አቅም ለመቀየር የተወሰደ እርምጃ ነው።
በዚህም ለውጭ አስተዳዳሪዎች በውጭ ምንዛሬ ይከፈል የነበረውን ከፍተኛ ክፍያ ማስቀረት ተችሏል። በተጨማሪም በመለዋወጫ እጥረትና በብልሽት ከሥራ ውጭ የነበሩ የባቡር ጎታች ሞተሮችንና የዕቃ መጫኛ ፉርጎዎችን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ጥረት ወደ ሥራ ማስመለስ ተችሏል።
የተቋሙ ለውጥ በአስተዳደርና በጥገና ብቻ ሳይገደብ፣ ወደ ባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍም እየተስፋፋ ነው። የደረጃ አንድ ኮንትራክተርነት ፈቃድ ማግኘቱና ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር የ10 ዓመት የትብብር ስምምነት መፈረሙ፣ በአገር ውስጥ የባቡር መሠረተ ልማት ዕቃዎችንና ማሽነሪዎችን ለማምረት አዲስ ዕድል ከፍቷል።
በተጨማሪም የ392 ኪሎ ሜትር የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልዲያ/ሐራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ባለሙያዎችና በተረከቡት ማሽነሪዎች እንደገና ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩ፣ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች በግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያሳይ ሌላ ማሳያ ነው።
በንግድና ሎጂስቲክስ ዘርፍም ባቡሩ የቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የተሽከርካሪ ጭነቶችና የቁም እንስሳት ወጪ ንግድ ማጓጓዣ አማራጭ ሆኗል። በገቢ ንግድ ደግሞ ማዳበሪያ፣ የምግብ ዘይትና ሌሎች ሸቀጦችን ወደ ደረቅ ወደቦች ለማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ለውጥ ከአንድ ተቋም የፋይናንስ ስኬት በላይ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በራስ አቅም ማስተዳደር፣ መጠገንና ማሳደግ የኢኮኖሚ ነፃነትንና የቴክኖሎጂ አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ያሳያል።
የባቡር ዘርፉ ትንሣኤ የሚለካው በትርፋማነት ብቻ ሳይሆን፣ በተገነባው የሙያ አቅም፣ በተቀነሰው የውጭ ጥገኝነት፣ በተሻሻለው የጭነት አገልግሎትና በአገሪቱ የሎጂስቲክስ አቅም ላይ በሚያመጣው ለውጥ ጭምር ነው።
