ተገልጋዮች የቀላል ባቡርና የከተማ አውቶቡስ አገልግሎትን በአንድ የክፍያ ካርድ እንዲጠቀሙ የሚያስችል የተቀናጀ አሰራር ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ደገፉ ገብረመድህን እንደገለጹት፣ ተገልጋዮች በባቡር የሚጠቀሙበትን ካርድ በአውቶቡስም እንዲሁም በአውቶቡስ የሚጠቀሙበትን ካርድ በባቡር መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት እየተዘረጋ ነው።
የተቀናጀውን የቴክኖሎጂ አሰራር ለማስጀመር ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ የግብዓት ማሰባሰብ ሥራውም በአብዛኛው መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በቀጣዮቹ አምስትና ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ዘመናዊው የተቀናጀ አሰራር ለመሸጋገር የታቀደ ሲሆን፣ ይህም የክፍያ አሰባሰብና የካርድ አጠቃቀምን በማቀናጀት የተሳፋሪዎችን ምቾት ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
