ሽምግልናና ግዝት በኢትዮጵያ

Date:

ተገኑ ፀጋዬ

በኢትዮጵያ ታሪክ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከነገሥታት ጋር በነበራት ቁርኝት ትልቅ ቦታ ይሰጣት እንደነበር በታሪካችን ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ የነበራትን ተቀባይነት ለማሳየት አያሌ ነገሮችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ለቤተክርስቲያን የሚሰጣት ክብር ከፍተኛ በመሆኑ ካህናት የሚያደርጉትን ሽምግልና፣ ምርቃት እንዲሁም ውግዘት ሕብረተሰቡ ያለመወላወል ይቀበለው ነበር፡፡

በተለይ ከሰለሞን ሥርወ መንግሥት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን የንግሥና ሥርዓት መቃወም በካህናቱ በሚሰጠው ግዝት ምክንያት ነገሥታቱ አይነኬ ሆነው እንዲዘልቁ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡

በዘመኑ የነበሩት ካህናት በሕዝቡ በነበራቸው ተቀባይነትና ተፈሪነት ለንጉሦቹም ፈተና የሆኑበት ጊዜም ነበር፡፡ በ1847 ንጉሠ ነገሥት ሆነው የተሾሙት ዐፄ ቴዎድሮስ ከካህናት ጋር ባለመግባባታቸው ፈተና ገጥሟቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ ለግጭቱ መነሻ ዐፄ ቴዎድሮስ ካህናቱ ከያዙት ሰፋፊ መሬት ይቀነስ ያለበለዚያ ግብር ይክፈሉ በማለታቸው ነበር ዐይንና ናጫ ለመኾን የበቁት፡፡ ጥቅማቸው የተነካባቸው ካህናት ታዲያ ሕዝቡን በንጉሡ ላይ እንዲሸፍት አድርገዋል ይባላል፡፡

እዚህ ላይ የምንረዳው ነገር ሕብረተሰቡ አምኖ ይተገብረው የነበረው ግዝት ይሁን እርቅ በፀጋ ተቅብሎ መተግበሩ አንድነቱን ጠብቆ እንዲኖር ረድቶታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሚሰማና የሚከበር አካል መኖሩ ከተሰመረለት መስመር እንዳይወጣ ሕብረተሰቡ አምኖ የተቀበለውን ነገር አለመቀበል እና መቃወም መገለል እንደሚያስከትል ያሳያል፡፡

አሁን ባለንበት ጊዜና ሁኔታ የመጨረሻ የሚሰማና የሚከበር አካል አለ ወይ? ሕዝቡ መንግሥትን ያምነዋል ወይ? የሃይማኖት መሪዎችንም በጥርጣሬ ነው የሚያየው ፤ ይኼ አለመተማመን ደግሞ ለሕግ ተገዢነት እየቀነሰ እንዲመጣ እንዲያውም ባለሥልጣናቱና የሃይማኖት መሪዎቹ ያላከበሩትን ሕግ ለተራው ሕዝብ ምኑ ነው ወደሚል መንፈስ እየመጣን ይመስለኛል፡፡

ወደ ተነሣሁበት ነጥብ ስመለስ በሀገራችን ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ግዝቶች መካከል ጎልተው የታዩትን ሁለቱን በጥቂቱ እንመልከት፡-

አንደኛው በታሪካዊነቱና በአርአያነቱ ምንግዜም በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወሰው የአቡነ ጴጥሮስ ግዝት ነው፡፡ በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የፋሺስት ጦር አዛዡ አቡነ ጴጥሮስን አስቀርቦ የሚጠየቁትን ትብብር የሚፈፅሙ ከሆነ ለህይወታቸው ዋስትና እንደሚሰጣቸው ቃል ይገባላቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሕዝቡ ከተሰበሰበ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ በተቃራኒው ሕዝቡ ለጣሊያን ፋሺስት መንግሥት እንዳይገዛና ባለው አቅም ሁሉ ወራሪውን ጠላት እንዲዋጋ ይህን ባያደርግ ግን እንደገዘቱት ቃላቸውን ሰጡ፡፡ በዚህ የፀና አቋማቸው! ላገራቸው ክብር ሲሉ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል፡፡

እዚህ ላይ አንድ የታሪክ ግጥምጥሞሽ እስቲ እንመልከት፡-

ጉዳዩ እንዲህ ነው በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ አስተባባሪ የነበሩት ጀነራል መንግስቱ ንዋይ በዙፋን ግልበጣ ክስ ስቅላት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ይታወቃል፡፡ እኚህ ግለሰብ በ1937 ዓ.ም በበላይ ዘለቀ ላይ የተበየነውን የስቅላት ፍርድ አስፈፃሚ ነበሩ፡፡ በወቅቱም የመቶ አለቅነት ማዕረግ ነበራቸው፡፡ ልብ አድርጉ ሁለቱም ግለሰቦች ክሳቸው ተመሳሳይና የተሰቀሉበትም ቦታ አንድ መሆኑን ልብ በሉ ፤ የስቅላቱ ሥፍራ ደግሞ ተክለሃይማኖት አደባባይ ላይ ነበር፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን ነገሥታት ቤተክርስቲያንና የሃይማኖት አባቶችን ለዙፋናቸው መጠበቂያ እንዴት ይጠቀሙባቸው እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡

ሌላው በበጎ ጎን የሚነሳው የሽምግልና ሥርዓት ነው፡፡ ይኸ በካህናት የሚከናወነው የሽምግልና ሥርዓት ፀብን በማብረድ ወደ እርቅ የሚመጡበት ሥርዓት ነው፡፡ የሚያስገርመው በሃይማኖት አባቶች ጣልቃ ገብነት የሚፈፀመው የእርቅ ሥርዓት ከሁለቱም ወገን ተቀባይነት ስለሚያገኝ ያለቅሬታ የሚፈፀም መሆኑ ነው፡፡

ይኽንን የመሰለ የሽምግልና ሥርዓት ከነበረን አሁን ሀገራችን ላይ ያለውን ግጭት እንዴት መፍታት አቃተን? አሁን ያለው ግጭትና አለመግባባት በምን መንገድ መፍታት ይቻላል? ሽምግልናውስ በማን ይከናወን? በአሁኑ ሰዓት የሚሰማና የሚከበር አካል አለ ወይ? ካለ መንግሥት ወይስ የሃይማኖት አባቶች? አለመግባባታችን እያደር እየሰፋ እርስ በእርስ ስንጋጭ ለምን መፍትሔ አላመጡም ወይስ ጉዳዩ የሚመለከተው የሰላም ሚኒስቴርን ስለሆነ ይሆን?

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል የተዋቀረው የሰላም ሚኒስቴር ሥራው ምን ይሆን? የተበጀለትን ገንዘብ እምን ላይ ይሆን የሚያውለው እጅግ የሚያስገርመው ይኸ ተቋም ከተዋቀረ ወዲህ ግጭቶች በፊት ከነበሩት በእጥፍ እጥፍ ጨምረዋል፡፡ ታዲያ ይኼ የሰላም ነው ወይንስ የግጭት ተቋም? ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ይባል የለ?

ቀድም ብዬ በመግቢያዬ ላይ ለማንሳት አንደሞከርኩት ቀደምት አባቶቻችን በግልም ይሁን በቡድን ለሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ለመፍትሔነት ይጠቀሙባቸው የነበረው ግዝትና የሽምግልና ሥርዓት የራሱ በጎ ጎን እንደነበረው ነው፡፡

በእርግጥ ስለግዝቶቹ ስናነሳ ነገሥታት ካህናትን በመጠቀም ሕዝቡን ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ መጠቀሚያ ያደርጉት እንደነበር ነው፡፡ ግዝቶቹ በአረዳድ ችግር መጥፎም በጎም ጎኖች ነበራቸው! ለንፅፅርም ሁለቱን ግዝቶች አይተናል፡፡

ይኼን ጉዳይ ሰፋ አድርገን ለማየት ብንሞክር ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱት ግጭቶችና አለመግባባቶችን ለመፍታት እንደቀድሞው የሽምግልና ሥርዓት ተጠቅመን መፍትሔ ማምጣት አቃተን? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ሽማግሌ ጠፍቶ ነው? ወይንስ የግጭቱ አካላት ሽምግልናውን ማክበር ተስኗቸው?

ከንጉሡ ከሥልጣን መወገድ ጀምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ለሕዝብ ቆመናል፣ ሀገራችንን ካረጀና ካፈጅ ሥርዓት አላቀን አዲሲቷን ኢትዮጵያን እንገነባለን ቢሉም መደማመጥ አቅቷቸው መድረኩን ከውይይት ይልቅ የድብድብ አድርገውት ለአያሌ ወጣቶች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኖ አልፏል፡፡ እንደዉም ስለእርቅ ሐሳቡም የተነሳ አይመስልም፡፡ በዚህ ምክንያት በዛ ዘመን የነበሩ አለመግባባቶች ተዳፍነው ቆይተው አሁን እንደ አዲስ ሀገራችንን የትርምስና የሰቆቃ አድርገዋታል፡፡

በተለይ በወቅቱ ተነስተው የነበሩት የብሔር መብት ጥያቄዎች ጊዜ ጠብቀው በመነሳታቸው ግጭቶች በየለቱ እየበረከቱ ሀገሪቱን አንደግመል ሽንት ወደኋላ አስቀርተዋታል፡፡

ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት የኾነው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን መመሥረቱ ጅማሮው እሰይ የሚያስብልና ወደ እርቅ ከመጣንና ከተግባባን ወደፊት ሀገራችን የተሻለ ሰላምና ዕድገት እንድትጎናፀፍ ይረዳታል፡፡

እዚህ ላይ ስለኮሚሽኑ አዎንታዊና አሉታዊ የሆኑ ጥያቄዎች በቡድንም በግለሰብም ደረጃ እየተነሱ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው ለችግሮቻችን መፍትሔ ሁሉንም ያማከለ የሽምግልና ሥርዓት መተግበር መሆኑ ሁላችንንም ያግባባናል፡፡

በተለይ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል ኮሚሽኑ ከየትኛውም ተፅዕኖ ነፃ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው ቀጥሎ አሁን ኮሚሽኑ ምን ውጤት ላይ ደርሷል? በየጊዜው የደረሰበትን ሁኔታ በየደረጃው ለምን ለሕዝብ ይፋ አላደረገም? የሚሉ ጥያቄዎች መከተላቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሕዝብም ጭምር ስለሆነ በተገቢው መጠን ለሕዝቡ መግለፅ ስላለበት፡፡ ሌላው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት እንዳላሳተፈ እየተነገረ ነው፡፡ ከዚህ የቅሬታ አቅራቢዎች አንዷ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ለምን ለሚለው ጥያቄ ኮሚሽኑ አጥጋቢ መልስ መስጠት አለበት ብለን እናምናለን ፤ ካለበለዚያ ምክክሩን ጎዶሎ ያደርገዋል፡፡

ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እንምንረዳው ከዚህ ቀደም በዓለማችን ከተደረጉት የእርቅ ሙከራዎች ውስጥ በተለይ በአፍሪካ ከፊሉ እንዳልተሳካ ነው፡፡

ለምን ብለን ከጠየቅን የተሞከሩት የእርቅ ክንውኖች የሕብረተሰቡን ፍላጎትና ሥነ ልቦና ያላገናዘቡ መሆናቸውና ለእርቅ የተቀመጡትም ተወካዮች ከተፅዕኖ ነፃ ያልሆኑ ከወከሉት ሕዝብ ይልቅ የግላቸውን ፍላጎት ለሟሟላት በሚያደርጉት ጥረትና ግትርነት ነው፡፡ በደቡብ ሱዳን የተደረጉ አያሌ የድርድር ሙከራዎች ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ማታ ለሰላም ተጨባብጠው ጠዋት ጦርነት አጃኢብ ነው፡፡

ስለዚህ ለጋራ ሰላማችን አብላጫውን ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀውን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባር እነዚህና የመሳሰሉትን የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎች በመነሳት ሕዝቡን እፎይ የሚያስብል ሥራ እንዲሠሩ የሚመለከታቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡

ለመልካም ስራ ረፍዶ አያውቅም!

ለኢትዮጵያ ሰላም ሁላችንም እንተባበር!

———-

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 218 ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ለሊት እንቅልፍ የለኝም

"አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ያሳስበኛል፤ እኔ አሁን 86 ዓመት...

አዎ ነበሩ ….

🔘የሁሉም አባት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሓጅ ዑመር🔘ነፍስዎ በሰላም ትረፍ "...

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስን ሳር ቅጠሉ የሚወዳቸው

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስን ሳር ቅጠሉ የሚወዳቸው የሀይማኖት...