በአሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን የሚቃወሙ ሠልፎች ተካሄዱ።
የተቃውሞ ሠልፉ የተዘጋጀው “ኖ ኪንግስ” በተባለ ቡድን አማካኝነት ነው።
ሠልፎቹ የተካሄዱት ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ ያዘጋጁትን ወታደራዊ ትርዒት በመቃወም መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ሠልፍ የተካሄደው በሎስ አንጀለስ እና በሌሎችም አካባቢዎች የፕሬዚደንቱ የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ተቃውሞ ከተነሳ ከቀናት በኋላ ነው።
የሕግ አውጭዎች፣ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች እና አክቲቪስቶች በኒውዮርክ፣ ፊላዴልፊያ እና ሂዩስተንን ጨምሮ የአሜሪካን ባንዲራ እና ትራምፕን የሚተቹ መፈክሮችን ለያዙ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ንግግር አድርገዋል።
ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የተካሄደው ወታደራዊ ትርዒት፣ የትራምፕ የልደት በዓልም ነበር፣ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት 250ኛ ዓመትን ለማክበር ያለመ ነበር።
ትራምፕ ትርዒቱን በመቃወም የሚካሄድ ማንኛውም ሠልፍ “ከባድ እርምጃ” እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዚደንቱ የአገሪቱ ጦር ለሰጠው አገልግሎት ባደረጉት አጭር ንግግር አመስግነዋል።
አክለውም “ወታደሮቻችን ተስፋ አይቆርጡም። አይማረኩም እንዲሁም በጭራሽ አያቋርጡም። ይዋጋሉ፣ ይዋጋሉ፣ይዋጋሉ። እናም ያሸንፋሉ፣ ያሸንፋሉ፣ ያሸንፋሉ” ብለዋል።
በአሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ትርዒት የተካሄደው በፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤችደብሊው ቡሽ የስልጣን ዘመን አሜሪካ በባሕረ ሰላጤው ያካሄዳቸውን ጦርነት ድል ለማክበር በሚል እአአ ሰኔ 1991 ነበር።
በወቅቱ በትርዒቱ ላይ 200,000 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የርችት ማብራት ስነ ስርዓቱን ደግሞ 800,000 ሰዎች መመልከታቸውን ኤልኤ ታይምስ ዘግቧል።
በቅዳሜው ዝግጅት ላይ አየሩ እርጥበታማ ስለነበር እና ዝናብ ይዘንባል የሚል ትንበያ በመኖሩ የታደሙት ሠዎች ቁጥር ከዚያ በታች ነበር።