በአዲስ አበባ በመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ቁጥጥር እየተደረገ ነው አለ የከተማዋ ንግድ ቢሮ፡፡
በቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በመዲናዋ ያለውን የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም በከተማዋ በሚገኙ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በስፋት ለተጠቃሚዎች እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ 219 የእሑድ ገበያዎች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች ተደራሽ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
የግብርና እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች በእሑድ ገበያዎች በስፋት እንዲቀርቡ የገበያ ትስስር መፈጠሩንም አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ምርት በሚደብቁና በሚያከማቹ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ልዩ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡
የቁጥጥር ሥራው እስከታችኛው መዋቅር መዘረጋቱን ጠቁመው ÷ ሕብረተሰብ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
አላስፈላጊ ዋጋ በመጨመር ብሎም ምርት በማከማቸት የገበያ አለመረጋጋትን ለመፍጠር በሚያሴሩ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ርምጃ ይወሰዳል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
(ኤፍ ኤም ሲ)