የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 20 ቀን 2019 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ በአጀንዳ ቅደም ተከተሉ መሠረት ጉባዔውን ቀጥሎ የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን ገለፀ።
በመጀመሪያ የተመለከተው ቀደም ሲል በአጀንዳ ተይዞ ለምልአተ ጉባኤ ቀርቦ የነበረውን የጋምቤላ ሀገረ ስብከትንና የቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳ ሀገር ሰብከትን የተመለከቱ አጀንዳዎች ሲሆን ፤ በወቅቱ የአጣሪዎች ሪፖርት በንባብና በቪድዮ መቅረቡን አስታውሰው ፤ በአጣሪ ልዑካን ከማስረጃዎች ጋር የቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎች፣ የሂሳብና ንብረት ቁጥጥር ሪፖርት ፣ ከሊቀውንት ጉባኤ ፣ ከሕግ አገልግሎትና ከሕግ አማካሪ የቀረቡ የውሳኔ ሐሳቦች በቅደም ተከተል ከቀረቡ በኋላ የአህጉር ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ለተፈጠሩት ጥፋቶች በጉባኤው ፊት በአካል ቀርበው ይቅርታ በመጠየቃቸውና ፣ የይቅርታ ጥያቄያቸውንም በቀረቡት የቀኖና ጥሰቶች፣ የአስተዳደርና ፣ የአሠራር ክፍተቶች በመጥቀስ የይቅታ ጥያቄያቸውን ለምልአተ ጉባኤው በጽሐፍ አቅርበዋል ።
ምልአት ጉባኤውም ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ያቀረበትን የይቅርታ ደብዳቤ በንባብ ከሰማ በኋላ በየርዕስ ጉዳዩ ተገቢውን የቀኖና እና አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት በስፋት በመወያየት የሚከተሉትን ወስኗል።
በዚህም መሠረት የብፁዕነታቸውን የይቅርታ ደብዳቤ በመቀበልና የቀኖና ውሳኔ በመስጠት ፤
አንደኛ ፡ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ለቀርቡባቸው የቀኖና ጉዳዮች እስከ ግንቦት 2019 ዓ/ም የርክበ ካህናት ምልእተ ጉባኤ ድረስ በየትኛውም ሀገረ ስብከት ሳይመደቡ በደብረ ሊባኖስ ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በጸሎትና በሱባኤ ተወስነው እንዲቆዩ ፣
ሁለተኛ ፡ ብፁዕነታቸው ለአህጉር ስብከት ማስረከብ ይገባቸው የነበሩ መኪኖችን ወደ ገዳም ከመሄዳቸው በፊት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅለይ ቤተ ክህነት እንዲያስረክቡ ፣
ሦስተኛ ፡ ከሂሰብ ጋር የተያያዘው በሚገባ ተጠርቶ እንዲቀርብ እና ዉሳኔ እንዲያገኝ ምልእተ ጉባኤው ወስኗል ብለዋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመቀጠል የተመለከተው ክፍት በሆኑ አህጉር ስብከት ብፁዓን አባቶችን መመደብ ሲሆን ፤ በዚሁ መሠረት ፡
አንደኛ ፡ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ለወደፊቱ አባት እስኪመደብ ድረስ የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከትን ደር,በው እንዲመሩ
ሁለተኛ ፡ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ዶ/ር) የጋምቤላ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ
ሦስተኛ ፡ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የሰቲት ሆመራና ወልቃይት ጠገዴ ሀገረ ስብከትን ደር,በው እንዲመሩ ፣ በማለት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል ብለዋል፡፡
አክለውም ምልአተ ጉባኤው የአዲስ አባባ ሀገረ ስብከትን የተመለከተ የአጣሪዎች ሪፖርት በንባብ በመሰማት ፣ የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስንና አብረው ይሠሩ የነበሩ የተወሰኑ የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን ምላሽ በማዳመጥ ወይይቱን ቀጥሏል ።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
