አማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ቢሰበስብም፣ አብዛኛዎቹ የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ባለማሳወቃቸው በቀሪ ጊዜያት እንዲከፍሉ አስጠነቀቀ።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ታዘባቸው ጣሴ ፤ ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት 100.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ እስከ መስከረም 27/2018 ዓ.ም በተሰበሰበው ዕለታዊ መረጃ መሠረት ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።
ይህ አፈጻጸም ቢኖርም፣ በክልሉ ካሉ 22,930 የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች መካከል በዚህ ሦስት ወር ውስጥ ግብራቸውን አሳውቀው የከፈሉት 4,004 ብቻ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
አቶ ታዘባቸው በርካታ ግብር ከፋዮች አሁንም
ግብራቸውን አሳውቀው እንዳልከፈሉ በመግለጽ፣ በቀሪ ጊዜያት ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።
የገንዘብ ሚኒስትር ከዚህ ቀደም በአዲሱ በገቢ ግብር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1395/2017 ላይ ማብራሪያ እንደሰጠዉ፤ በየሶስት ወሩ የሚከፈለው ግብር ተፈጻሚ የሚሆነው ግብር ከፋዩ የሂሳብ ሪፖርት ከሚያቀርብበት ወር መጨረሻ ጀምሮ ካለው የሶስት ወር ጊዜ በኋላ በሚኖረው የ30 ቀን ጊዜ ውስጥ ነዉ ማለቱ ይታወሳል።
CapitalNews