በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና ባውሚት ኦስትሪያ መካከል በነበረው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቃቸው የ3D ኮንክሪት ፕሪንት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ኮርፖሬሽኑና ባውሚት ኦስትሪያ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ስምምነት ፈጽመዋል
*
ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ረሻድ ከማልና የባውሚት ኦስትሪያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ኤድዋርድ አርትነር ተፈራርመዋል፡፡
የባውሚት ኦስትሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ኤድዋርድ እና የባውሚት አፍሪካና ኤዥያ ብቸኛ ወኪል የሆነው የካሳ ዲ አርጂላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ሮላንድ ጃንሰን የጫካ ሳተላይት ከተማ ፕሮጀክትን ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እተከናወኑ ያሉትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ያከናወነውን የቅድመ ዝግጅት ስራም ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ሁለንተናዊ አመራር ሰጭነት ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ተምሳሌት ሀገር በመሆኗ በቤት ልማት ዘርፍ በቴክኖለጂ አቅርቦት ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚያደርግም ነው የባውሚት ኦስትሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ኤድዋርድ የገለጹት፡፡
ተዘዋውረው በተመለከቱት አስደናቂ አገራዊ የልማት ሥራና ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ በኮርፖሬሽኑ በኩል በተከናወኑት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መደሰታቸውን ገልጸው የ3D ኮንክሪት ፕሪንት ቴክኖሎጂ አቅርቦት በአጭር ጊዜ ለመፈጸም ስምምነት ላይ ለመድረስ ኩባንያቸው መወሰኑን ሚስተር ኤድዋርድ ተናግረዋል፡፡
የ3D ተክኖሎጂ ቤትን በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት በአጭር ጊዜ በማቅረብ የኢትዮጵያን የቤት አቅርቦት ከመሰረቱ እንደሚቀይረው ያላቸውን እምነት ሚስተር ኤድዋርድ ገልጸዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በ3D ኮንክሪት ፕሪንት ቴክኖሎጂ ለሚገነቡት ቤቶችን ባውሚት ኦስትሪያ የገንዘብና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ድጋፍ እንደሚያደርግም ሚስተር ኤድዋርድ ገልጸዋል፡፡
የባውሚት ኦስትሪያ አፍሪካና የኢዥያ ወኪል ካሳ ዲ አርጅላ በአንድ ዓመት ውስጥ የ3ዲ ኮንክሪት ቴክኖሎጂን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ሚስተር ኤድዋርድ ተናግረዋል፡፡
የባውሚት ኦስትሪያ 3D ኮንክሪት ተክኖሎጂ አቅርቦትና ተከላ ፣ የእውቀት ሽግግር እና ሥልጠና ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት የወቅቱ የከተሞች ዋናኛ ችግር የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ከመሰረቱ ለመቅረፍ ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ላይ ኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቤት ከመገንባት ወደ ማምረት የሚያስችለንን የ3ዲ ኮንክሪት ቴክኖሎጂን ትገበራን በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ከባውሚት ኦስትሪያ ጋር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ እና የአገራዊ ቤት ልማት እቅድን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነቱ ትልቅ ሚና እንሚኖረው ክቡር አቶ ረሻድ ተናግረዋል፡፡