ክፍል 2
ግዮን መጽሔት :- የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ቀለል ያሉ የቅራኔ መተንተኛ መሣሪያዎችን ለወጣቶች ማስተዋወቅ ነው፤ በዚህ ጽሁፍ ክፍል አንድ የቅራኔ ደረጃዎችን (Conflicts Stages) ተመልከተናል። በዚህኛው ክፍል 2 ደግሞ የቅራኔ ካርታ (Conflict Mapping) እና የቅራኔ ዛፍ (Conflict Tree) እንመለከታለን። በሚቀጥለው ክፍል ሦስት የቅራኔ ሥርዓት ትንተና (Systems Conflict Analysis.) እናቀርባለን። ከዚህ በፊትም እንዳደረግው የቅራኔ መተንተኛዎቹን ለመግለጽ ኢትዮጵያን በምሳሌነት እንጠቀማለን። ኢትዮጵያን የተጠቀምነው ለምሳሌ ያህል ብቻ ነው። አንባቢ መሣሪዎቹን ተጠቅሞ ማንኛውንም (ትልቅም ይኹን ትንሽ) ቅራኔ መተንተን፤ የኢትዮጵያንም ሁኔታ ከተለየ አቅጣጫ መመልከት ይችላል (ትችላለች)።
1. የቅራኔ ካርታ
በክፍል አንድ እንደተመለከትነው እያንዳንዱ ቅራኔ አለመጣጣም (incompatibility)፣ ተዋናዮች (actors) እና ተግባራት (actions) አሉት። የቅራኔ ካርታ ዋነኛ ትኩረት ተዋናዮች ላይ ነው። “ጠቡ በማንና በማን መካከል ነው?” የሚለው ጥያቄ ቀላል ቢመስልም እጅግ አወዛጋቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ። አብዛኛውን ጊዜ ቅራኔ ውስጥ የገቡ አካላት ተፋላሚዎቻቸውን የሚገልጹባቸው ቃላት በስሜትና ስም ማጥፋቶች የታጀቡ በመሆናቸው ለሰከነ የቅራኔዎች ጥናት የሚመቹ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት የትግራይ ኃይሎች የፌደራልና የአማራ ክልል ኃይሎችን፤ የፌደራል መንግሥት ደግሞ የትግራይ ኃይሎችን የሚገልፁበት መንገድ መከተል ለሰከነ የቅራኔ ጥናት የሚመች ካለመሆኑም በላይ ጠቡ በትክክል በማን እና በማን መካከል እንደሆነ ለማወቅ እንድንቸገር ያደርገናል። ስለሆነም የቅራኔ ካርታ ለመሳል “ቅራኔው ውስጥ ያሉት ዋና ዋና ተዋናዮች እነማን ናቸው?” የሚለውን ጥያቄ በተቻለ መጠን ከፍረጃ ቃላት በነፃ መንገድ መመለስ ያስፈልጋል። “ተዋናዎች” ሲባል ዋናዎቹ ተፋላሚዎች ማለት ብቻ አይደለም፤ በፍልሚያው ውስጥ በጎም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ድርጅቶች ወይም አገሮች ጭምር ናቸው። ይህም ከጀርባ ሆነው ዋናዎቹን ተፋላሚዎችን በሀሳብ፣ በፋይናንስ፣ በድርጅት፣ በፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ፣ ካስፈለገም በአድቮከሲና ዲፕሎማሲ የሚረዱ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ድርጅቶችና አገሮችን ሁሉ ይመለከታል።
“የተዋናዮቹ አንፃራዊ ኃይል” በቅራኔ ካርታ ውስጥ ማየት የምንሻው አቢይ ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው የተዋናዮች አንፃራዊ ኃይል በየጊዜው ሊቀያየር የሚችል፤ አንዳንዴም ለመገመት አስቸጋሪ የሆነ ነገር ነው፤ ያም ሆኖ በአጥኚው እምነት እና ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት ተዋንያን የራሳቸውን ውሳኔ የማስፈፀም አንፃራዊ አቅማቸው አመላካቶች ሊኖሩ ይገባል። ተውናዮች የተናገሩትን ወይም የዛቱትን የመፈፀም አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ አመላካቾች ማስቀመጥ ያስፈልጋል።
በተዋናዮች መካከል ያለው የርስበርስ ግኑኝነት ማማላከት የቅራኔ ካርታ እምብርት ነው። በተዋናዮች መካከል ያለው ግኑኝነት የወዳጅነት ይሁን የጠላትነት መለየት አለበት፤ ከዚህም አልፎ የወዳጅነት ወይም የጠላትነት መጠንን አመላካቶች ማስቀመጥ ጠቀሜታ አለው።
ከላይ የተዘረዘሩትን መረጃዎች የያዘ በጥንቃቄ የተሠራ የቅራኔ ካርታ ማን፣ የት ቦታ፣ ምን ቢያደርግ ቅራኔውን ለማርገብ እንደሚረዳ ፍንጭ ይሰጣል። የተዋናዮች ዓይነትና አንፃራዊ ጉልበት፤ የቅራኔው ጭብጥ፤ በተዋናዮች መካከል ቅራኔዉን በተመለከተ ያለው የርስበርስ ግኑኝነት እና የቅራኔው ደረጃ በየጊዜው የሚቀያየር በመሆኑ የቅራኔ ካርታ አንዴ ተሠርቶ የሚያበቃ ሳይሆን ሁኔታዎች በተቀያየሩ መጠን መስተካካል ያለበት በየጊዜው የሚሻሻልና የሚቀያየር የቅራኔ እድገትን መከታተያ መሣሪያ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች (እንዲሁም ማናቸውም በሰላም ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች) የቅራኔዎች ተለዋዋጭ ባህሪያትን የሚከታተሉበት የራሳቸው ካርታ ሊኖራቸው ይገባል። በሚገባ የተዘጋጀ ካርታ ከሌላቸው በእውቀት ላይ የተመሠረተ የሰላም አጽተዋጽዖ ለማድረግ ይቸግራቸዋል፤ እንዲያውም ጠብ ለማብረድ ብለው የሚያደርጉት ተግባር ባላሰቡት መንገድ ጠብ የሚባብስ ሊሆን ይችላል።
ከዚህ በታች የቀረበው ስዕል 1 ኢትዮጵያ አገራችን በአሁኑ ወቅት ከገጠሟት ቅራኔዎች ሁለቱን የሚያመላክት የቅራኔ ካርታ ለአስረጂነት ቀርቧል። አስር እጅግ የተለያዩ አቅሞች ያሏቸው ክልሎችን እና የፌደራል መንግሥት እንዲሁም ከ50 በላይ በዚህ ቅራኔ ውስጥ ድርሻ ያላቸውን የፓርቲካ ድርጅቶች፣ ሁሉም የእምነት ተቋማት፣ መደበኛና ኢመደበኛ ሚዲያዎች፣ በእነዚህ ቅራኔዎች ውስጥ በተለያዩ መንገዶች እጃቸው ያለበት የውጭ አገራት መንግሥታትና ዓለቀፍ ድርጅቶች እና ሌሎችን ተዋንያን መሳል ስለሚኖርብን በአንድ አነስተኛ ገጽ ማድረግ የሚቻል አይደለም። በዚህም ምክንያት ስዕል 1 የቀበረው ለመልመጃነት ብቻ መሆኑን እና የካርታውን ውስብስብነ ለመቀነስ ተዋናዮቹ የፊደራልና የክልል መንግሥታት ብቻ እንደሆኑ ተደረጎ መወሰዱን ልብ ይሏል።
ስዕል1፡ የኢትዮጵያ የቅራኔ ካርታ (ለመልመጃነት የቀረበ)
ከላይ በስዕል አንድ የቀረበው የኢትዮጵያ ቅራኔ ካርታ በርካታ ዋና ዋና ተዋንያን (ለምሳሌ የውጭ አገራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የአገር ውስጥ መደበኛ ሚዲያዎች፣ የውጭ አገራት መደበኛ ሚዲያዎች፣ ሶሻል ሚዲያን መሰል ኢመደበኛ ሚዲያዎች፣ ዓለም ዓቀፍ የዕረዳታ ድርጅቶች እና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች) ያልተካተቱበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ዛሬ ስለገጠማት ችግሮች በግምት ከሚሰጥ በተሻለ ምስል ይሰጣል። ስዕልን አንድን የተመለከተ ታዛቢ የሚከተሉትን ወዲያውኑ ይገዘነባል።
- የፌደራል መንግሥትና ዘጠኙ ክልሎች በአንድ በኩል እና ትግራይ በሌላኛው ወገን የሆኑበት ደም አፋሳሽ ግጭት ያለ መሆኑ (ቅራኔ አንድ)፣
- በክልል መንግሥታት መካከል ቅራኔ መኖሩ (ቅራኔ ሁለት)፤ ይህ ቅራኔ በአብዛኛው ግጭት አልባ ቢሆንም አልፎ አልፎ በድንበር እና በከተሞች ይገባኛል ጥያቄዎች ሳቢያ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ያስከተሉ መሆናቸው፣ እና ።
- በተዋንያኑ (በዚህ ምሳሌ በክልሎች) መካከል ከፍተኛ የኃይል መበላለጥ መኖሩ።
በእነዚህ ካርታውን ያጠና ግለሰብ በቀረቡት መረጃዎች መነሻነት የሚከተሉት አስተያየቶችን ይሰነዝር ይሆናል።
- የፌደራልና የክልል ኃይሎች ጥምረት ከትግራይ ጋር የገቡበት ጦርነት ለማሸንፍ እንዲችሉ በመካከላቸው ያለው ቅራኔ ማርገብ አለባቸው።
- የትግራይ ኃይሎች የገቡበትን ጦርነት ለማሸነፍ በክልሎች መካከል ያለውን ቅራኔ ማጋጋላቸው መሆኑ የማይቀር ነው።
- በክልሎች መካከል ያለው ቅራኔ ካልተፈታ ከትግራይ ጦርነት ማብቃት በኋላ እንኳን አገሪቷ ሰላም አደጋ ላይ ሊወደቅ ይችላል።
- በክልሎች መካከል ያለው የኃይል መበላለጥ ምክንያቱ ተጠንቶ መፍትሔ ማግኘት ለሁለቱም ቅራኔዎች ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ የፌደራል አወቃቀሩን እንደገና ማጤን ይፈልጋል።ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በ ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን የፕሮግራምና አጋርነት ዋና ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡
ሐሳብና አስተያየቶች በinfo@ycdfet.org ወይም tkersmo@yahoo.com ሊያደርሷቸው ይችላሉ፡፡
የዚህን ፁሑፍ ቀጣይ ክፍል በዚህ ሳምንት መጨረሻ እናቀርባለን ።
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 235 ነሐሴ 2018 ዓ.ም
