መነኮሳቶቻችን ወዴት ሄዱ?

Date:

በሊቀሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ

ምንኩስና በፈቃድ ነው “ምንኩስናሰ ዘእምፈቃድ ይዕቲ ወአኮ ዘእምአገብሮ፤ ምንኩስናስ የፈቃድ ናት እንጅ የግድ አይደለችም” እንዲል መጽሐፉ። እነዚያ በመጽሐፍ ያሉት መነኮሳት ወዴት ሄዱ? ሊሾሟቸው ሲሉ በረሀ ገብተው የሚሠወሩት። ሹመትን እንደ እግዚአብሔር ቀን ፍርድ የሚፈሩት ምን ዋጣቸው?

የምንኩስና ሕጉ ራስን ለመከራ ማዘጋጀት እንዲገባ ያዝዛል እንጅ ራስን ለሹመት ለሽልማት ማደላደል አይደለም። ምክንያቱም “ልጄ ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ወደ ገዳም ብትሄድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ” ተብሎ ተጽፏልና። አሁን ከልክ አለፈ። በማይሞላ ፍላጎቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን እየፈተነ ያለ መነኩሴ ሁሉ ቢችል ወደ ገዳሙ ይመለስ።

የካደውን ዓለም ፍለጋ መግነዙን ፈቶ የሚመለስም ካለ ይመለስ። ንስሐ ገብቶ ምዕመን ሆኖ እንዲኖር ቤተ ክርስቲያን ትፍቀድለት። የሚበላውን የሚጠጣውን ለማግኘት ብሎ ምዕመናንን ግራ ከሚያጋባ የወደደውን ቤተ ክርስቲያን ታድርግለት። የሚነዳው መኪና ለማግኘት ምዕመናንን ወደ ገሐነም እየነዳ ከሚወስዳቸው መኪናውን ይዞ ይሂድ።

ለብፁዓን አባቶቻችን እግረ መንገዴን ጥያቄዬን ላቅርብ።

እኔ በእናንተ ጸሎትና ቡራኬ ተጠብቄ የምኖር ደቀ መዝሙራችሁ ብሆንም የቤተ ክርስቲያን ጉዳት በተሳለ ችንካር እንደተወጋ ሰው የሚያሳምመኝ ያለ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሌላ ዓላማ የሌለኝ ልጃችሁ ነኝ።

ዛሬ ለመጣብን ፈተና መፍትሄው

* ሥርዐተ ሢመተ ክህነት

* ሥርዐተ ምንኩስና ሲጠበቅና የትምህርት ቤቶቻችንን ያሉበትን ሁኔታ መከታተል ስንችል ነው ብየ አምናለሁ።

ይሄ የግራኝ ዘመን አይደለም። የተማረ ሳይጠፋ ወይም አስተምረን ማብቃት ስንችል የተገኘው ሁሉ ቅስና ዲቁና የሚሾመው እስከመቼ ነው? ሃይማኖቱን በሚገባ ያልተረዳና የሚያገለግለውን ቁርባን ከምድራዊ መብል መጠጥ መለየት ያልቻለ ሰው ስንሾም ብዙ ዘመን ሆነን። ተጎዳን እንጅ አልተጠቀምንም። ከሾምነው በኋላ በቀኖናው ልክ ለማድረግ ከምንጥር በቀኖናው ልክ አድርገን ልንሾመው ይገባል።

ቤተ ክርስቲያናችን (ክብር ለቀደሙን አባቶቻችን ይሁንና) ዲያቆን፣ ካህን ከዚያም በላይ ሊሾም ሚወድ ቢኖር መቼ መሾም እንዳለበት ተጽፏል። ገበያ በመጣበት ክህነት ተሹሞ ገዳም ደርሶ ሊመጣ በሄደበት እግረ መንገዱን መንኩሶ እየመጣ ከቀጠልን ስንበጠበጥ መኖራችን የማይቀር ነው።

ምዕመናን የሚያስተምር አባት፣ ጥያቄአቸውን የሚመልስ መምህር ይፈልጋሉ ነገር ግን በትምህርት ቤቶቻችን ላይ ዘመኑ የሚፈልገውን ጥንቃቄ ካላደረግን ዛሬ እንደ ትናንቱ አይደለም። የተማረውን ትምህርት በሽያጭ ካልሆነ በነጻ መስጠት የማይፈልግ መምህር ይመጣብናል። ምዕመናን ካልከፈሉ በቀር አገልግሎት የማያገኙበትን ሁኔታ እየተመለከትን ነው ለዚህ መድኃቱ ጉባኤ ቤቶቻችንን መመልከት ከቻልን የሚገኝ ይመስለኛል።

ምንኩስናችንም ልክ ሊኖረው ይገባል። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለምናኔ አብነት የምትሆን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጥሬ ቆርጥመው፣ አሸዋ ላይ ተኝተው፣ ማቅ ለብሰው፣ ሰንሰለት ታጥቀው የሚያገለግሉ መናንያን በየገዳማቱ መኖራቸውን አውቃለሁ። ዛሬም እንደ እንጦንስ እንደ መቃርስ የሚኖር መነኩሴ ቢፈለግ የሚገኘው በኛ ገዳማት ውስጥ ብቻ ይመስለኛል። በበረሀ ወድቀው ሌትና ቀን ሰማያዊ ጸጋን ብቻ በመሻት የሚተጉ አገልጋዮች አሉንና።

ነገር ግን በከተሞች የምናየው የአንዳንድ መነኮሳት ሕይወት አሠረ ምንኩስናን የተከተለ አይደለም። የትምህርታቸው የምንኩስና ሕይወታቸው ሳይስተካከል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሹመት በእጃቸው ለማስገባት ሲጋፉ ስናያቸው በየሀገራችን እንገረማለን። የአድባራት የገዳማት አስተዳዳሪ ከመሆናቸው በፊት በገዳም ረድዕ ሆነው ማገልገል አለባቸው። ዳቤ ጋግረው እንጨት ለቅመው እግር አጥበው ምናኔውን ከአበው በተግባር ተምረው ከመጡ ብንሾማቸው ይገባቸዋል። ሥርዐተ ምንኩስናችንም የሚያዝዘው እንዲሁ ነውና። ለሹመትም ሆነ ለሌላ አገልግሎት ቤተ ክርስቲያን ካልፈለገቻቸው ከገዳም መውጣት ሕጉ አይፈቅድላቸውም። መነኩሴ ለደጅ ጥናት ከገዳም ያለ ሊቀ ጳጳሱ (ኤጲስ ቆጶሱ) ፈቃድ የሚወጣበት ዘመን ቢኖር የኛ ዘመን ነው። እንደ ሰማሁት ከሆነ ግብጻውያን ዛሬም ሊቀ ጳጳሱ ሳይፈቅድላቸው ከገዳማቸው አይወጡም።

በሕግ በሥርዓት መሠረት ካላመነኮስናቸው ያለ ቀኖናም ቢሆን ሹመት ካገኙ መሾማቸው አይቀርም። እያየን ያለነውም ይህንኑ ነው። አያሳዝንም በየጎጡ ሿሚ ከተገኘ ጵጵስናን ያኽል ትልቅ ሹመት ብድግ አድርጎ መሸከም? አሁን የመጣብንን ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ፈተና ሹመቱን ሽልማቱን ንቀው ቢመነኩሱ ኖሮ አናየውም ነበር። ለዚህ መፍትሔው አሁንም የምንኩስና ሥርዐቱን ሳያውቁ በአመክሮ ሳይፈተኑ ለምን እንደሚመነኩሱ ሳይጠየቁ ዓለምን ንቀው ሳይሆን ዓለምን ፈርተው የሚመነኩሱ እንዳይሆኑ ከገዳማውያኑ እና ከሊቃውንቱ ጋር በመሆን ሥራ መሥራት ይገባል።

ገዳማቶቻችን በመነኮሳት እጦት እየተሰቃዩ ከተሞችን በመነኮሳት አጣበን የምንኖር ከሆነ ነገም በሌሎች ክልሎች ፈተናው ይቀጥላል።

ቀድሞ በዓለም ኃዘን ሲገጥመን ገዳም ሂደን ከአበው በረከት ተቀብለን ከኃዘናችን ተጽናንተን እንመለስ ነበር አሁን ግን ያልመነኑ መነኮሳት ኃዘን ሆኑብን።

በስንክሳር ያነበብናቸው፤ በዜና አበው የተመሰጥንባቸው ዓለምን በቃል ኪዳናቸው ያስባረኩልን መነኮሳት ወዴት ሄዱ? ያስብላል።  መጻሕፍትን የጻፉልን፤ ሃይማኖት ያጸኑልን ሰውን በምግባር ያነጹልን ዕውቀት ከምናኔ አስተባብረው የያዙ መነኮሳት ወዴት ጠፉብን? በተለይ የኛ ቤተክርስቲያን ታላላቅ ሐዋርያት መነኮሳት ነበሩ። በጉባኤ ተገኝተው የተከራከሩ፤ ጉባኤ አስፍተው ደቀ መዝሙር ሰብስበው ቀለም የነገሩ መነኮሳት ሊቃውንት ነበሩ። ብራና የዳመጡልን ቀለም ያወጡልን መጻሕፍትን የጻፉልን የጨለማው ዘመን ላይ ብቅ ብለው ወርቃማ የሥነ ጽሑፍ ዓመት ያስቆጠሩን ሊቃውንት መነኮሳት ነበሩ። ቤተክርስቲያኒቱ በድርሰት የሞሏት መነኮሳት ዛሬ እንደማታ ጀንበር አቆልቁለውብን ተቸገርን። አሁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና ምዕመናን መነቃቀፉንና መተቻቸቱን ትተን ለመፍትሔ የሚሆን ሐሳብ በማቅረብ ወደ ነበርንበት የምንመለስበትን ቀን ማቅረብ እንድንችል እጠይቃለሁ።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...