(በእውቀቱ ስዩም)
በዚህ ዓለም ላይ እንደ ዘፋኝ የታደለ የለም፤ አንድ ነጠላ ዜማ ሰርተህ ድርብርብ ህይወት ትኖራለህ፤ ስቴድየም ሙሉ ታዳሚ ታስጨፍራለህ፤ ታዋቂ ዘፋኞች ባንድ መድረክ የሚያገኙት ገንዘብ የኢትዮጵያን ህዝብ አመታዊ በጀት ያክላል ቢባል ማጋነን ይሆናል፤ ዘፋኝ መንግስተ ሰማያት አይገባም የሚባለው አለምክንያት መስሎሀል? ዘፋኞች የመንግስተ ሰማያት ድርሻቸውን እዚህ ምድር ላይ ጨርስዋል፤ ሁለቴ መንግስተ ሰማያት የለም፤
ይብላኝ ለገጣሚ! እውነተኛ ሰማእታት ማለት እኛ ነን ፤ እልም ባለው ወበቅ “ስካርፍ” እምንለብሰው ወደን አይደለም፤ ሆድ ቢብሰን ለመታነቅ እንዲያመቸን ነው፤
ይህ በእንዲህ እያለ፥ ባለፈው ግሪንላንድ ሚባል አህጉር ውስጥ የሚኖር አንድ ዲያስፖራ የግጥም ምሽት እንዳዘጋጅ ጋበዘኝ ፤
“ የፕሌን ትኬት ታሰናዱልኛላችሁ?”
“በጀት የለንም ! እንደ ፍራሽ የሚነፋ ጀልባና የሚያሻግሩህ ሰዎችን አዘጋጅተናል” ሲለኝ ሙያየን ጠላሁት፤
ባለፈው ደግሞ “አላስካ” የተባለ ጠቅላይ ግዛት ሄድኩ፤ አላስካ ማለት ሩሲያዎች “ብርድ ያስመታናል “ብለው ለአሜካኖች የሸጡላቸው ያገር መስኮት ነው፤
ካውሮፕላን ስወርድ አንድ ብርቱ ዲያስፖራ ተቀበለኝ፤ “አበባ ይዘው የሚጠብቁኝ ቆነጃጅት ጠብቄ ነበር ’ አልሁት፤
‘ወገኛ ነህ ባክህ! እዚህ አገር አመቱን ሙሉ ክረምት ነው፤ ካገራችን ከወጣን ወዲህ አበባ አይተን አናውቅም ፤ “ አለና የምጎትተውን ሻንጣ ብድግ አርጎ አሸከመኝ፤
“እሺ አበባውስ ይቅር፤ የቆነጃጅቱስ ነገር? “ አልሁት፤
“ሲጀመር ቆነጃጅት ከሆኑ ስንት እድል እያላቸው እዚህ፥ የግዜር ፍሪጅ የሆነ አገር ለምን ይመጣሉ? እኛም ካናዳ የለመግባት ስንሞከር ተቆርጠን ቀርተን ነው” አለኝና መኪናው ውስጥ ገፍትሮ አስገባኝ ፤
በጥሩንባና በነጋሪት ተቀስቅሶ ለዝግጅቴ የመጣው ዲያስፖራ አስራ ሁለት አይሞላም፤ ፕሮሞተሩ ለዶዶራንት መግዣ የሚበቃ ቀብድ ሰጠኝ ፤ ዝግጅቴን ለመታደም ከመጡት ሰዎች ፥ልጅ ሚካኤል ሲያትል ላይ ሲዘፍን ያጀቡት ፖሊሶች በቁጥር ይበልጣሉ፤ አብዛኞቹ አሳ ሲያጠምዱ፥ ለዶልፊን አክሮባት ሲያለማምዱ፥ ሻርክ ሲበልቱ ውለው ስለመጡ ከፍተኛ ድካም ይነብባቸዋል ፤
የገቡት አብዛኞቹ እኔ እያነበብሁ እንደ ሰነፍ ተማሪ ዴስካቸው ላይ ተኝተዋል፤
ከዝግጅቱ በሁዋላ አዘጋጁን ካጠገቤ አጣሁት ፤ በስንት ፍለጋ ከአዳራሹ ጀርባ ባለው ባር ውስጥ ጅን በበረዶ እየጣጣ ሲያለቅስ አገኘሁትና፥ ለበረዶው ከፍየ አጽናንቼው ዞር ስል፤
“በውቄ “ አለኝ ፤
“ወየ”
“ ቅድም ከሰጠሁህ ቀብድ ላይ ትንሽ ልታበድረኝ ትችላለህ? “
