በሐኪሞች የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት ታስረው በሚገኙ ባለሙያዎች ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም  ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

Date:

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የሐኪሞች የሥራ ማቆም አድማ እንዲሁም አድማውን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር በዋሉ ባለሙያዎች ላይ በእስር ቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል።

በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ክትትልና ምርመራ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ሙሉጌታ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ በሥራ ማቆም አድማው የሁሉም ዜጎች መብት እንዲከበር በንቃት እየተከታተለ ይገኛል።

ኢሰመኮ የመንግሥት አካላት በአድማው ላይ የሰጡትን ምላሽ እየተከታተለ የሚወሰደው እርምጃ ተጨማሪ የመብት ጥሰት እንዳያስከትል ክትትል እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

ጉዳዩን ለመፍታትም ኢሰመኮ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ ከጤና ባለሙያዎች ተወካዮች እና ከሌሎች የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውሰዋል። 

አክለውም “በፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የሕክምና ባለሙያዎች አያያዝን አስመልክቶም ክትትል በማድረግ ላይ እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን ቤተሰብ እንዳይጎበኝ መከልከሉን አስመልክቶ፤ የተነሱ ስጋቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ መገኘቱንም አቶ ዮናስ ጠቁመዋል።

የሕክምና ባለሙያዎችን ከተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ከጥቅማጥቅም፣ ከሙያ እድገት ዕድሎች እንዲሁም ከምቹ የሥራ ቦታ እና የሥራ ቦታ ነጻነት ጋር የተያያዙ ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎችን ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጤና ሚኒስቴር ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም ‘መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች በተሰጠው 30 ቀናት አልፈጸመም’ በሚል ከግንቦት 5 ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ‘በማኅበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳ አድርገዋል፣ በሌሎች በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰዋል እንዲሁም በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል’ ያላቸውን 47 የሕክምና ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የመብት ጥያቄ ያነሱና የሥራ ማቆም አድማ ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን ከመንግሥት ጋር ለማደራደር ጥረት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የሕክምና ባለሙያዎች አያያዝን አስመልክቶም ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተሰረቀ ዕቃ በቅናሽ ዋጋ መግዛት ወይም ይዞ መገኘት እስከ 3 ዓመት እስራት ያስቀጣል

በርካሽ ዋጋ የተሰረቁ ስልኮችን፣ ላፕቶፖችንና ሌሎች ዕቃዎችን መግዛት፣ የተሰረቀ...

በኢትዮጵያ በዓመት ከ18ሺህ በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር ይጠቃሉ ተባለ

ጤና ሚኒስቴር  ከለሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የጡት ካንሰር...

35ኛው ዓለም አቀፍ የስኳር ህመም ቀን ተከበረ

በዝግጅቱ ላይ የስኳር ህመምን ለመከላከል ቅድመ ምርመራን፣ ጤናማ አመጋገብንና...

በኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማእከል

መገናኛ ብዙሃን ሕጋዊ እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ...