በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በመኪና ማቆሚያ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት በባንክ ጥበቃ ሰራተኛ በጥይት የተመታው ወጣት ሕይወቱ ማለፉ ተገለጸ።
በቦሌ አካባቢ በካርን ሳፊል እና በአስራት ሕንፃዎች አቅራቢያ በሚገኝ የባንክ ተቋም ፊት ለፊት የመኪና ማቆሚያን በተመለከተ በወጣቱና በባንኩ ጥበቃ ሰራተኛ መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተነግሯል።
ወጣቱ ተሽከርካሪውን አቁሞ ወደ ሌላ ጉዳይ ከሄደ በኋላ ሲመለስ አለመግባባቱ ወደ ግጭት ተቀይሮ የጥበቃ ሰራተኛው ተከታታይ ተኩስ መክፈቱን የዓይን እማኞች መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በጥይት ተመትቶ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ወጣቱ ወደ አያት ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱን ማዳን እንዳልተቻለ ተገልጿል።
ድርጊቱን የፈጸመው የጥበቃ ሰራተኛም ከክስተቱ በኋላ መሳሪያውን ጥሎ ለመሸሽ መሞከሩን የዓይን እማኞች መግለጻቸው ተጠቅሷል።
በመኪና ማቆሚያ ምክንያት በተነሳ አለመግባባት የአንድ ወጣት ሕይወት ማለፉ በአካባቢው ከፍተኛ ሀዘን ፈጥሯል።
