ፈያ የተቀናጀ የልማት ድርጅት (FIDO) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ለሚገኙ ከ180 ሺህ በላይ ዜጎች የሚውል የ1.9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አዲስ የሰብዓዊ ድጋፍ ፕሮጀክት በዛሬዉ እለት በይፋ አስጀመረ።
ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወናቸውን የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች በገመገመበትና አዲሱን ፕሮጀክት ይፋ ባደረገበት መርሐ-ግብር ላይ እንደተገለጸው፣ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፈንድ (EHF) የገንዘብ ድጋፍ ለቀጣይ አንድ ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
የድርጅቱ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንበሱ ቶላ እንደገለጹት፣ ድጋፉ በድርቅና በግጭት ለተጎዱ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን ፕሮጀክቱ በጤና፣ በሥነ-ምግብ፣ በንጹሕ መጠጥ ውሃና አካባቢ ንጽሕና፣ በግብርና፣ በጥበቃ እንዲሁም በባለብዙ ዓላማ የገንዘብ ድጋፍ ዘርፎች ላይ ተቀናጅቶ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
ፈያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባከናወናቸው ሦስት ፕሮጀክቶች ከ600 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ውስጥም በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፈንድ በኩል በተገኘ 4.55 ሚሊዮን ዶላር በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በኦሮሚያ ክልል ከ295 ሺህ በላይ ዜጎች የምግብ፣ የንጹሕ ውሃ፣ የጊዜያዊ መጠለያና የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ፈያ ያሉ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሩቅና ድንገተኛ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመንግሥትን ጥረት በማገዝ የላቀ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ነዉ የተገለፀዉ።
አዲሱን ፕሮጀክት ከፈያ ጋር በአጋርነት የሚተገብረው የሲቄ የሴቶች ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተርም፣ የአገር በቀል ድርጅቶች ቅንጅታዊ አሰራር በጾታ ላይ የተመሠረተ ጥቃትን ለመከላከልና ተጋላጭ ወገኖችን በዘላቂነት ለመደገፍ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ላለፉት 25 ዓመታት በልማትና ሰብዓዊ ድጋፍ ዘርፍ ሲሰራ የቆየው ፈያ የተቀናጀ የልማት ድርጅት፣ ይህንን አዲስ ፕሮጀክት ከመንግሥት ተቋማት፣ ከማኅበረሰቡና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እንደሚያስፈጽም ተገልጿል።
