የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ አሜሪካ ውስጥ ለሕይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ በመፈጠሩ እንዲወጣ መደረጉን የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ‘ሺን ቤት’ አስታወቀ።
የደኅንነት ተቋሙ ባወጣው መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያ ልጅ ያኢር ኔታኒያሁ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከፍተኛ ስጋት መኖሩን መገምገሙን እንዲሁም “ከጥበቃ ቡድኑ ጋር በአስቸኳይ ከአሜሪካ ወጥቶ ወደ እስራኤል እንዲመለስ” ውሳኔ ላይ መደረሱን ገልጿል።
ነገር ግን ሺም ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ልጅ ደኅነንት ላይ ስጋት ስለደቀነው ጉዳይ ምንነት ያለው ነገር የለም።
ይህ ውሳኔ ይፋ የሆነው አንድ ዘገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ ፍሎሪዳ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት የኢራን የግድያ ሴራ ዒላማ ሆኖ እንደነበረ ካመለከተ በኋላ ነው።
አባቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የመንግሥታቸው ደጋፊ ከሆነው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ ላይ “ኢራን ከልጆቼ አንዱን ዒላማ አድርጋለች። ከልጆቼ መካከል አንዱን ለመግደል ሞክራለች” ሲሉ ከስሰው ነበር።
ኒውስማክስ የተባለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ረቡዕ ዕለት ባሠራጨው ዘገባ የደኅንነት ተቋማት ጥቃቱ ሊፈጸም የነበረው በኢራን ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ ብሎ ነበር።
ያኢር ኔታኒያሁ ለበርካታ ዓመታት ማያሚ ውስጥ ኖሯል። በኑሮውም ቅንጡ ሕይወትን የሚመራ ሲሆን በእስራኤል የደኅንነት አባላት ጥበቃ ይደረግለት ነበር።
ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ ጋዛ ውስጥ ጦርነት እያካሄደች በነበረበት ጊዜ እስራኤላውያን ጦር ሠራዊቱን ሲያገለግሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ ግን ከአገር ውጪ ይኖራል የሚል ትችት ሲቀርብባቸው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጃቸው አሜሪካ ውስጥ የሚደረግለትን ጥበቃ በተመለከተ ለቻናል 14 በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ጥበቃው ባይደረግለት ኖሮ ገዳዮቹ “ይሳካላቸው ነበር” በማለት ተከላክለዋል።
የቀኝ ክንፍ አክቲቪስት የእና የፖድካስት አቅራቢ ሆነው ያኢር ኔታኒያሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በንቃት የሚሳተፍ ሲሆን፣ በእስራኤል ፖለቲካ ላይ አስተያየት ከመስጠት በተጨማሪ የአባቱን የፖለቲካ ተቀናቃኞች፣ የመንግሥታቸው ተቺዎችን እና ጋዜጠኞችን በማጥቃት ይታወቃል።
