“ወጣቶች ሀገራቸውን የሚረዱበትና ራሳቸውን የሚያበቁበት ማዕቀፍ ነው”

Date:

በቀጠሮአችን መሰረት ዛሬ የአቶ ዜናዬነህ ግርማ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል። ድርጅታቸው ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› በመጪዎቹ ዐሥር ዓመታት የሚተገበር፣ የትኩረት ማዕከሉንም በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በሚገኙ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 35 ዓመት በገጠር በከተማ በትምህርትና ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ወጣቶች ላይ ያደረገ መሪ ዕቅድ (ስትራቴጂክ ፕላን) ይፋ አድርጓል፡፡

ለመኾኑ ይኽ በብዙ መልኩ አምራች የሚባለውን የማኅበረሰብ ክፍል ለመለወጥ የተነደፈ ዕቅድ ምን ምን ይዘቶችና ግቦች አሉት ስንል ከድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዜናዬነህ ግርማ የሚከተለውን ቆይታ ከግዮን ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር አድርገዋል፡፡ መልካም ንባብ!


ግዮን፡- እነዚህ ስድስት ስትራቴጂያዊ ግቦች ምን ምን እንደኾኑ በዝርዝር ቢያስረዱን?


ዜናዬነህ፡- የመጀመሪያው ከወጣቶች ጋር የምንሠራቸው ሥራዎች የእነሱን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማሳደግ ነው፡፡ ይሄ የተለያዩ ማዕቀፎች አሉት፡፡ ማዕቀፉ የወጣቶቻችንን የእይታ አድማስ ማስፋት ነው፡፡ በክሎትና፣ በእውቀት እና በሥልጠና ማብቃት ነው፡፡

የእነርሱን ዘላቂ የኾነ የተቃና ሕይወት ጉዞ እንዲሠንቁ ለማስቻል እንሠራለን፡፡ ይህን ስናደርግ የእነርሱን የሥነ-ምግባር እና የአመለካከት ለውጥ እንገነባለን፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውንም እንዲወጡ ለማስቻል እንጥራለን፡፡ በዚህም የአግረ ኢንተርፕሪነር ሺፕ ሥልጠና፣ የህይወት ክህሎት ሥልጠናዎች፣ የኮሚኒኬሽን እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥልጠናዎች፣ የአመራር ሥልጠናዎች፣ ኮቺንግ እና ሜንቶር ሺፕ ሥልጠናዎች በሙሉ በዚህ ውስጥ ይሠጣል፡፡

ይህን ስናደርግ የወጣቶችን አቅም የሚያሳድጉ ነገሮችን በምንሠራባቸው ክልሎች የልህቀት ማዕከላት ለማቋቋም አስበናል፡፡ በዚህም ሂደት ወጣቶች ሀገራቸውን የሚረዱበትና ራሳቸውን የሚያበቁበት ማዕቀፍ ነው፡፡


ሁለተኛው ስትራቴጂ እቅድ ዘላቂ የሆነ የወጣቶች የሠላም ሥራዎችን ለመስራት የተለያየ የሰላም ኢንተርፕራይዞች መፍጠር ነው፡፡ የተለያዩ የሠላም ግንባታ ተነሳሽነት እንዲሁም ዘላቂ የሆነ የግጭት አፈታት አቅም ማጎልበት ሥራዎችን አብረን እንሠራለን፡፡

ለምንም ነገር የማይበገር በስነ አእምሮ ጠንካራ የሆነ ወጣት ለመፍጠር እንሠራለን፡፡ ሦስተኛው ስትራቴጂ እቅድ የምንለው ደግሞ ወጣቶች ምቹና ተገቢ የኾኑ አገለግሎቶችን እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡

በተለይ ሁለገብ ጤናቸውን በተመለከተ በአካልና በአእምሮ የበቁ ወጣቶችን ለመፍጠር እንሠራለን፡፡ ከዚህ በፊት ባለፉት አራት ዓመታት ወደ 11 የሚጠጉ ምቹ የሆኑ የወጣት አገልግሎቶች የምንሰጥባቸው ተቋማት ነበሩን፡፡ በቅርቡም ወደ 4 የሚጠጉ ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር አገልግሎቶቻችንን ለወጣቱ ተደራሽ ለማድረግ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል፡፡


አራተኛው ስትራቴጂያዊ ግብ ወጣቶች በፖሊሲ እቅድና ግብ ደረጃ እነሱን በሚመለከቱ ሁለንተናዊ ነገሮች ሁሉ ባለቤት ኾነው የሚተገብሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንሠራለን፡፡ ወጣቶች ስለራሳቸው የሚጠይቁበትን፣ የሚወስኑበትንና መሰል ሁነቶችን የሚያስተናግዱበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ያን ለማድረግ አጠቃላይ የኾነ የወጣቶች አድቮኬሲ ሥራዎችን እና ድምፃቻቻን ከፍ እሚያደርጉበት ሁኔታቸውን እናመቻቻለን፡፡ በዚህም የወጣቶች ተሟጋችነትና የፖሊሲ ተሳትፎ እንዲያጎሉ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡
አምስተኛው ስትራቴጂያዊ ግብ ባለፉት 10 ዓመታት በደንብ ያልሠራንበት ብለን በጥናት የለየነው ወጣቶች ዘላቂ የባሕል ጥበቃና ልማት እንዲያደርጉ ማብቃትን በሚመለከት ነው፡፡

ብዝኃነት አለን፡፡ በዚህ ብዙኃነት የወጣቶች ዘላቂ የባሕል ጥበቃ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ ድርጅታችን በትኩረት ይሠራል፡፡ በዚህ ውስጥ ዘላቂ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ እንዴት ይመጣል የሚለው አንዱ ነው፡፡ ወጣቶች በዩኒሰኮ የተመዘገቡ የባህል ቅርሶቻችን እንዲጠበቁ የሚያስችል ሥራ እንሠራለን፡፡ በዚህ ዙሪያ ሚዲያውም ይረዳናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡


የመጨረሻውና ስድስተኛው ስትራቴጂያዊ ግብ የሚያተኩረው የወጣቶችን ማኅበራዊ ተሳትፎ ማጉላት ላይ ነው፡፡ ወጣቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲያዳብሩ እንጥራለን፡፡ በሌላ በኩል ወጣቶች ለማኅበረሰባቸው የሚያበረክቷቸው ተሳትፎዎች እንዲጎለብቱ ለማድረግ እንጥራለን፡፡

ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው ስድስት ነጥቦች ዋና ዋና የተቋሙ ግቦች ኾነው እንደ ትኩረት አቅጣጫ ተቀምጠዋል፡፡ ይህን ተፈፃሚ ለማድረግ የተለያዩ አጋሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የተለያየ ሀብትና የሰው ኃይል ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ከቀድሞዎቹ አጋሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን በመቀጠል ከሌላው ጋር ደግሞ አዲስ ግንኙነት የምንፈጥርበት ሁኔታ ላይ እንሠራለን፡፡


ግዮን፡- እነዚህን እቅዶች የት የት አካባቢ ነው ተግባራዊ የምታደርጉት?


ዜናዬነህ፡- ከዚህ በፊት በ5 ክልሎች ላይ እንሠራ ነበር፡፡ በዚህም ከክልል መንግሥታት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ እናም በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ እየሠራን ነበር፡፡ አሁን ግን በትግራይና አማራ ክልሎችም በሠፊው ለመሥራት አቅደናል፡፡


ግዮን፡- የምትሰጧቸው አገልግሎቶች ከክልል ክልል ይለያያሉ?


ዜናዬነህ፡- ሥራውን ሳንጀምር የምናከናውናቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች ለይተናል፡፡ ከዚህ አንፃር የትኛው ክልል ምን ፍላጎት አለው፤ ወይም የትኛው አጋር የትኛውን ክልል ወይም ፕሮጀክት ማገዝ ይፈልጋል የሚለውን ለመለየት የፕሮጀክታችን ዲዛይን ይወስነዋል፡፡

ለምሳሌ አዳዲሶቹ ክልሎች በጦርነት ውስጥ የቆዩና ብዙ ጉዳቶችን ያስተናገዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ በርካታ ድርጅቶች አሉ፡፡ እኛ ደግሞ የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የሰላም ተደራሽነት ላይ እንሠራለን፡፡ ወጣቶች ሰላምን በማፅናት ከሃይማኖትና ሲቪል ተቋማት ጋር በመኾን እንዲሠሩ አቅደናል፡፡


ግዮን፡- ተቋማችሁ ራሱን ችሎ ከመዝለቅ አኳያ ካለፈው የሥራ ሒደታችሁ የአሁኑ በምን ይለያል?


ዜናዬነህ፡- በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ልንደርስባቸው የሚገቡ የማኅበረሰብ ሥራዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች እድሜያቸው ከ15-35 በገጠርና በከተማ ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በግጭት ቀጠና አካባቢ ጉዳት ያጋጠማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ነው፡፡

በዚህ አገልግሎታችን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና የአካባቢው አጋሮችም ጭምር ይጠቀማሉ፡፡ የአሁኑ የስትራቴጂክ ዕቅዳችን የሚለየው የሀብት አሰባሰባችን መንገዱ ነው፡፡ የዓላማችን ማስፈፀሚያ ከዚህ ቀደም ስንከተለው ከነበረው አካሄድ ለወጥ በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነት በሚያጎላ መንገድ አቅደናል፡፡


የድርጅቱን ዘላቂነት ለማስቀጠል እኛ በየትኛው ሥራ ላይ እንሰማራለን የሚለውን ስናስብ ግብርና ላይ ብናተኩር የበለጠ ወጣቶቻችንን ተጠቃሚ እንደምናደርግ ተረድተናል፡፡ ለዚህም የንግዱ ማኅበረሰብ አብሮ የሚያግዝበትን መንገድ አመቻችተናል፡፡

ለምሳሌ አሁን ላይ በርካታ ባንኮች ከእኛ ጋር ለመሥራት ንግግር ጀምረዋል፡፡ ከተወሰኑት ጋር የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርመናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለአቢሲኒያ፣ አዋሽ፣ ወጋገንና ሌሎችም ባንኮች ፕሮፖዛል አዘጋጅተን በንግግር ላይ እንገኛለን፡፡

ከእኛ ጋር አብረው መሥራት የሚፈልጉ ሌሎች በርካታ ተቋማትም አሉ፡፡ ሌላው የተማርነው ነገር ፕሮጀክት እንደሚመጣውና እንደሚሄደው ሁሉ የውስጥ ገቢ ሲጠናከር ራሱን ሲችል በሁሉም መልኩ የድርጅቱ እና ሰራተኞቹ ተጠቃሚት ከፍ እንደሚል ነው፡፡


ግዮን፡- ከሰላም ሚኒስቴርና ከሥራና ፈጠራ ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች መሰል የመንግሥት ተቋማት ጋር አብራችሁ እንደምትሠሩ ተጠቁሟል፡፡ በምን መልኩ ነው ከእነዚህ ተቋማት ጋር አብራችሁ የምትሠሩት?

ዜናዬነህ፡- ማንኛውም ሥራ ሲሠራ የመንግሥት አጋርነት የግድ ነው፡፡ የትኛውም ፕሮጀክት ብቻውን አይሠራም፡፡ ሥራ የሚሰጥ፣ የሚደግፍና የሚከታተል አካል ይኖራል፡፡ መንግሥት ከእኛ ጋር የሚሠራው በመቆጣጠርና በመገምገም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

የወጣቶች ሥልጠና ስናስብ እና መሰል ነገሮችን ስንሠራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያግዙናል፡፡ የሰላም ግንባታን ከወጣቶች ጋር ስንሠራ ከሰላም ሚኒስቴር እና ከቤተ ዕምነቶች ጋር በመነጋገር ነው፡፡ ሴቶችና ሕፃናት ግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃና ሌሎችም ላይ በጋራ የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ከመንግሥት ጋር ብቻ ሳይኾን ከሃይማኖት ተቋማትም ጋር አብረን እንሠራለን፡፡

ሌሎች ማኅበራቶችም አሉ፡፡ የትምህርት ተቋማትም አብረውን ይሠራሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም በጥናትና ምርምር እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር አብረውን ይሠራሉ፡፡ የተቋማትን ግብዓት በመጠቀም በጋራ እንሠራለን፡፡ እንዲህ ዓይነት የአጋርነት መንፈስና ለአንድ ዓላማ በጋራ መምጣት ሥራችንን ይበልጥ ያቀላጥፍልናል ያሳድግልናል፡፡


ግዮን፡- ትኩረታችሁ የትኞቹ ወጣቶች ናቸው? የአካል ጉዳተኛ ወጣቶች አካታችነት እንዴት ታዩታላችሁ?

የዚህን ጥያቄ መልስና የመጨረሻ የሆነዉን ክፍል የፊታችን ቅዳሜ ህዳር 13 -2018 ዓ.ም ይጠብቁን።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...