- በዘንድሮው ስብስብስ ውስጥ ዶናልድ ትረምፕ እና ኤሎን መስክ ተካተዋል
ዝነኛው እና ተፅእኖ ፈጣሪው ታይም መፅሄት በዘንድሮው የ ‘100 ተፅእኖ ፈጣሪዎች’ ዝርዝር ውስጥ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ኢትዮጵያዊውን ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖምን አካተተ።
በዘንድሮው የታይም መፅሄት ዝርዝር ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ባለሀብቱ ኤሎን መስክ እና የእንግሊዙ ጠ/ሚር ኬር ስታርመር መካተታቸው ታውቋል።
ዶ/ር ቴድሮስ በዚህ ዙርያ ማምሻውን የማህበራዊ ሚድያ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ሀሳብ “በዝርዝሩ ውስጥ መካተቴ በምሰራበት የአለም ጤና ድርጅት ውስጥ ለሚሰሩ ባልደረቦቼም እውቅና ነው” ያሉ ሲሆን በአለም ዙርያ በየቀኑ ግጭት ባሉባቸው ስፍራዎች ጭምር የጤና አገልግሎት ለማዳረስ የሚሰሩ ሰራተኞችን አስታውሰዋል።
በመፅሄቱ ላይ ስለ ዶ/ር ቴድሮስ ተጋባዥ ፀሀፊ በመሆን ያስነበቡት ዶ/ር ላሪ ብሪሊያንት የተባሉ የፈንጣጣ በሽታ ከአለማችን እንዲጠፋ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ሳይንቲስት መሆናቸውን መሠረት ሚድያ ተመልክቷል።
“ዶ/ር ቴድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ሀላፊ ከሆኑ በኋላ የአለማችንን የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀይረውታል፣ ይህ ደግሞ በበሳል አመራር እና ሳይንሳዊ በሆነ የውሳኔ አሰጣጥ የታገዘ ነበር። ዶ/ር ቴድሮስ ለአለም ጤና ስጦታ ናቸው” ያሉት ዶ/ር ላሪ በ194 ሀገራት የሚገኙ ሰዎችን ጤና የመጠበቅ ሀላፊነትን እየተወጡ የሚገኙ ብለዋቸዋል።
“አመራሩ መርህ ያለው ነው፣ ሀቀኛ ነው፣ ውጤት ተኮርም ነው። የአለማችን ህዝብ ከበፊት ግዜ በበለጠ ጤነኛ እንዲሆን አድርገዋል” በማለት ዶ/ር ላሪ ታይም መፅሄት ላይ አስነብበዋል።
በታይም መፅሄት መሪዎች (Leaders) ምድብ ከዚህ ቀደም ቀዳማዊ ሐይለ ሥላሴ እና ጠ/ሚር አብይ አህመድ ተካተው ነበር። ይሁንና ‘የታይም የአመቱ ሰው (Time Person of the Year) የሚለውን ማዕረግ ግን ያገኙ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ቀዳማዊ ሐይለ ሥላሴ ሲሆኑ ግዜውም እ.አ.አ በ1936 ጃንዋሪ ወር ነበር።
@MeseretMedia
