ጨቅላ ሕፃናት በሚታመሙበትና ወደ ሆስፒታል ማጓጓዝ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የአምቡላንስ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር የጨቅላ ሕፃናት፣ ሕፃናትና የዕድገት ዴስክ አስተባባሪ አቶ መለሰ ሰለሞን፤ አምቡላንስ ለእናቶችና ለድንገተኛ የጤና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለጨቅላ ሕፃናትም እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
አዲሱ መመሪያ አምቡላንስ መቼ፣ የትና ለምን ዓላማ መዋል እንዳለበት፣ የአገልግሎት አሰጣጡንና የቅብብሎሽ ሥርዓቱን በግልጽ የሚያስቀምጥ ሲሆን፤ ከታለመለት ዓላማ ውጭ በሚጠቀሙት ላይ ተጠያቂነትን የሚያስከትል አሠራርም ተካትቶበታል።
የአምቡላንስ እጥረትና ሌሎች ተግዳሮቶች ቢኖሩም ሕፃናት አስቸኳይ ሕክምና ሲያስፈልጋቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ እስከ ታችኛው የማኅበረሰብ መዋቅር ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ ጥሩ ጅማሬ ቢኖረውም ይበልጥ ለማጠናከር ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠበቁ አቶ መለሰ አስታውቀዋል።
