ህንድ የ1.4 ቢሊየን ህዝቦቿን ጥቅም ለማስጠበቅ “ምርጥ ስምምነት ካገኘችበት” ከየትኛውም ቦታ ነዳጅ ዘይት መግዛቷን እንደምትቀጥል በሩሲያ የሀገሪቱ አምባሳደር ተናግረዋል።
አምባሳደር የቪናይ ኩመር ይህንን መግለጫ የሰጡት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ ነዳጅ ዘይት ህንድ በመግዛቷ 50 በመቶ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ እና የጦር መሳሪያ ግዢ በመፈፀሟ የ25 በመቶ ቅጣትን ጨምሮ የቀረጥ ህጉ ሊጀምር መሆኑ መሰማቱን ተከትሎ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እንዳሉት ትራምፕ በህንድ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ታሪፎችን በሩሲያ ላይ “አጣዳፊ የኢኮኖሚ ጥቅም” ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እና በዩክሬን ያለውን ጦርነት እንድታቆም ለማስገደድ በማለም እርምጃውን ወስደዋል ብለዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኒው ዴሊ የጨመረው ርካሽ የሩሲያ ድፍድፍ ምርት ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት በማሻከር በንግድ ድርድሩ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
እ.ኤ.አ. በ2024 ህንድ ከገዛችው ነዳጅ ዘይት ውስጥ ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ነው። በ2021 ህንድ ከሩሲያ የገዛችው ነዳጅ ዘይት ግን 3 በመቶ ብቻ ነበት። ዩናይትድ ስቴትስ ህንድ ከሩስያ ነዳጅ ዘይት መግዛቷ ለዩክሬን ጦርነት የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ነው ሲሉ ወንጅለዋል። ኒው ዴሊ ግን ክሱን ሀሰተኛ ስትል አስተባብላለች።
በሞስኮ የህንድ አምባሳደር ኩመር ለሩሲያ ታስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ህንድ በንግድ ገበያ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ እና ቅድሚያ የምትሰጠው ለሕዝቧ የኢነርጂ ደህንነት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ ሁለተኛ ደረጃ ታሪፍ ለመጣል መወሰናቸው ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ያልሆነ በማለት የህንድ አቋምን ደግመዋል። የኩማር መግለጫ የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤስ ዣሻንካር ህንድ ኩሩስያ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት መግዛቷን ትክክለኛ ውሳኔ ሲሉ ከተከላከሉ ከሰዓታት በኋላ የተሰማ ነው።
